አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህግ ማስከበር ዘመቻ የተሰማራው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሁሉም አቅጣጫ ድልን በመጎናጸፍ ወደ መቀሌ እየገሰገሰ እንደሚገኝ በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የህብረት ዘመቻ ዋና መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ሃላፊ ተወካይ ብርጋዴል ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው የሰራዊቱን የህግ ማስከበር ዘመቻ አጠቃላይ ገጽታ በምስል አስደግፈው ገለጻ አድርገዋል።
ብርጋዴል ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው እንዳሉት፤ ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን የመንግስትን በትረ ስልጣን በሃይል ለመቆጣጠር በማለም በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ከፍተኛ ክህደት ፈጽሟል።
በዚህም የሀገር መከላከያ ሰራዊት የህወሃትን ጁንታ ጥቃት በመቀልበስ በከፍተኛ ቁጭትና ወኔ የህግ ማስከበር እርምጃውን በድል እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
“በምዕራብ ግንባር ከዳንሻ በመነሳት በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጦ ባእከር፣ ሁመራና ሽሬን መቆጣጠር ችሏል” ብለዋል።
“ከባድመ፣ ጾረና እና ዛላንበሳ የተነሳው ሰራዊት ደግሞ በከፍተኛ ድል አዲግራትን ተቆጣጥሮ ወደ መቀሌ እየገሰገሰ ይገኛል” ብለዋል።
ከራያና ጭፍራ በሁለት አቅጣጫ የተነሳው ሰራዊትም የደቡብ ግንባር ሲሆን፤ ሰራዊቱ ጨርጨር ላይ በመገናኘት በመሆኒ አድርጎ ከመቀሌ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ሔዋና መጠጋቱን ገልጸዋል።
ጽንፈኛ ቡድን ጥቃቱን ሲፈጽም የትግራይ ህዝብ ከጎኑ እንደሚሰለፍ አስቦ እንደነበር ገልጸው፤ ህዝቡ ግን “በችግር ጊዜ ከጎኔ የነበረውን የአገር መከላከያ አልወጋም” በማለት በተቃራኒው ለሰራዊቱ ድጋፉን ማሳየቱን አብራርተዋል።
ሰራዊቱ ለትግራይ ህዝብ ክሊኒክና ትምህርት ቤት ከመስራት ባለፈ አንበጣና ኮሮናን በመከላከል ሰፊ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበርም አስታውሰዋል።
የህወሃት ጁንታ በተለይ በሰሜን የትግራይ አካባቢ ለሚገኙ ነዋሪዎች “ሰራዊቱን እንዲወጉ” መሳሪያ አስታጥቆ እንደነበርም ብርጋዴል ጀኔራል ተስፋዬ ገልጸዋል።
ሆኖም የሀገር መከላከያ ሰራዊት አካባቢውን ሲቆጣጠር ነዋሪዎች ደስታቸውን ከመግለጽ ባለፈ በነቂስ በመውጣት የታጠቋቸውን መሳሪያዎች ለሰራዊቱ እንዳስረከቡ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
“ጽንፈኛ ቡድን በህዝቡ ድርጊት በመበሳጨቱም የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያን በዶዘር በማረስ ከጥቅም ውጭ አድርጎት ሄዷል” ብለዋል።
ይህም ቡድኑ ለትግራይ ህዝብ ምን ያህል ንቀት እንዳለው ያሳየበት እኩይ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።