አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጃፓን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታዎች ዙርያ ከኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት አካሄደ።
ውይይቱን የመሩት አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን መንግስት በትግራይ ክልል እያደረገ ያለው ዘመቻ ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ማስጠበቅን፣ ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ እንዲሁም ትጥቅ ማስፈታትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅን ያቀደ የህግ ማስከበር እርምጃ መሆኑን አስረድተዋል።
በህውኃት ሲፈጸሙ የነበሩ ተደጋጋሚ ህገ-መንግሥታዊ ጥሰቶችን መንግሥት በትዕግሥትና በሠላም ለመፍታት ቢጥርም ሀገራዊ ልዑላዊነትን በበዳፈር በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የተወሰደው እርምጃ ዘመቻው እንዲካሄድ ማስገደዱን አብራርዋል።
ዘመቻው ሲጠናቀቅ እንዲሁም ነጻ በወጡ አካባቢዎች ጊዜያዊ አስተዳዳር ተመስርቶ ህዝቡን መልሶ ለማቋቋምና ለመርዳት ዝግጅት መጠናቀቁን የገለፁ ሲሆን ወደ ሱዳን የተሰደዱትንም መልሶ ለመቀበልና ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን መግለፃቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በጃፓን ነዋሪ ሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ትክክለኛ መረጃዎችን ለጃፓን ሚዲያና ጃፓናውያን እንዲያደርሱ እና ለመልሶ ማቋቋም ጥረቱ በገንዘብና በቁሳቁስ አስተዋጽኦ እንዲያበርክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
በመንግሥት በኩል ተከታታይ፣ ተዓማኒና ተደራሽ የሆኑ መረጃዎች እንዲሰጡ፣ የህግ ማስከበር ሂደቱ በተቻለ ፍጥነት እንዲጠናቀቅ፣ ንጹሐን ዜጎች ተጎጂዎች እንዳይሆኑ ጥንቃቄ መወሰድ እንዳለበት እና በዘላቂ ሰላምና መልሶ ማቋቋም ላይ በትኩረት እንዲሰራ የሚሉ ሀሳቦችንም ተሳታፊዎቹ ቅርበዋል።