አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ያገኘችው የገንዘብ ድጋፍ የኢኮኖሚ ጥራትን ለማምጣት እንደሚያግዝ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ባለፉት 15 አመታት ኢኮኖሚያዊ እድገት ብታስመዘግብም የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ግን መገንባት ግን አልቻለችም።
ግብርና መር የሆነው መዋቅራዊ ሽግግር ከንግግር ወርዶ በተግባር ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ለምጣኔ ሀብቱ መጎልበት ሚናውን አለመወጣቱ ለዚህ እንደምክንያት ይነሳል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አግኝታለች።
የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ሲሳይ ረጋሳ አይ ኤም ኤፍ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረጉ ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው መልካም ጅምር መሆኑን ያነሳሉ።
ገንዘብ አጠቃቀሙ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል የሚሉት ዶክተር ሲሳይ፥ በብድር የሚገኝ ገንዘብን በምንዛሬ ለመክፈል በሚደረግ ሂደት የገንዘብ አለመመጣጠን በመፍጠር ፈተና ሊፈጥር እንደሚችል ይናገራሉ።
በብድርና ድጋፍ የሚገኘው ገንዘብ ባልተመጣጠነ የወጪና ገቢ ንግድ የተጎዳ ኢኮኖሚን ለመታደግ የሚውል ከመሆኑ አንጻርም፥ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ውሳኔ ለኢትዮጵያ ወሳኝ ሁነትን የጠበቀ ያደርገዋልም ነው ያሉት።
ዶክተር ተሾመ አዱኛ በበኩላቸው የውጭ ሀገራት ብድርም ሆነ ድጋፍ የኢኮኖሚ ጥራትን ለማምጣት ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ሀገሪቱ በምታገኘው ብድር ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማከናወን ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸውም አንስተዋል።
አሁን ላይ የተገኘው ገንዘብ ለመንግስታዊ የስርዓት ማዘመኛዎች ከመዋሉ አንጻር ሽንቁሮችን ለመድፈን አቅም እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል።
ሌላኛው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዶክተር ተስፋዬ ጮፋና ደግሞ በገንዘቡ አጠቃቀም ላይ በቂ ጥናት አድርጎ ወደ ተግባር መግባት ይገባል ባይ ናቸው።
የምርት መጠን መጨመር ለሀገሪቱ እድገት ወሳኝ መሆኑን የሚያነሱት ዶክተር ተስፋዬ፥ በራስ አቅም የኢኮኖሚ ችግሮችን ነቅሶ ከማውጣት ባለፈ ምርትን ማሳደግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አንስተዋል።
ምሁራኑ የግል ባለሃብቱ በኢኮኖሚው ጠንክሮ መውጣትና ተሳትፎውን ማሳደግ እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከተለያዩ ሀገራትም ሆነ አበዳሪ ተቋማት በሀገሪቱ ስም የሚመጡ ሀብቶች በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዲውሉ መደረግ ይኖርበታል ያሉት ምሁራኑ፥ ባክኖ ሲገኝም ለተጠያቂነት መስራት እንደሚገባ ያነሳሉ።
ከምንም በላይ ግን የኢኮኖሚውን ችግር በመቅረፍ በተለይም ለወጣቱ ሰፊ የስራ እድል መፍጠር እንደሚገባም አውስተዋል።
በሃይለእየሱስ መኮንን