Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ትራምፕ በፔንሲልቫንያ ያቀረቡት ክስ ውድቅ ተደረገባቸው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፔንሲልቫንያ ግዛት ምርጫው ተዛብቷል በሚል ያቀረቡት ክስ ውድቅ ተደረገባቸው፡፡

ትራምፕ በግዛቲቱ በፖስታ ወይንም “ሜይል ኢን ባሉት” የተሰጡ በሚሊየን የሚቆጠሩ ድምጾች ውድቅ እንዲደረግላቸው ነበር ክስ ያቀረቡት፡፡

ሆኖም ጉዳዩን የተመለከቱት ማቲው ብራን የተባሉት ዳኛ በትራምፕ የቀረበው ክስ ጭብጥ የሌለው ነው በማለት ውድቅ አድርገውታል፡፡

ዳኛው ትራምፕ እንዲታገድላቸው የጠየቁት ድምጽ ሰባት ሚሊየን እንደነበር ነው የገለጹት፡፡

ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በግዛቲቱ ትራምፕን ከ80 ሺህ በላይ ድምጽ በመያዝ ይመሯቸዋል፡፡

ዳኛው የትራምፕን ክስ ውድቅ ማድረጋቸው ተከትሎ በሚቀጥለው ሳምንት በፔንሲልቫንያ ግዛት ለጆ ባይደን የአሸናፊነት ሰርተፊኬት እንደሚሰጣቸው ይጠበቃል፡፡

እስካሁን መሸነፋቸውን ያላመኑት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ተጨባጭነት የሌለው ክስ እያቀረቡ እንደሚገኙ እየተነገረ ይገኛል፡፡

ከትናንት በስተያ በአሜሪካዋ ጆርጂያ ግዛት ዳግመኛ በተካሄደ የድምጽ ቆጠራ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ማሸነፋቸው ይፋ ሆኗል፤ ሆኖም ትራምፕ ለሦስተኛ ጊዜ ድምጽ ይቆጠርልኝ ማለታቸውም ተሰምቷል፡፡

አሜሪካኖቹ “ባትል ግራውንድ” በሚሏቸው እና ፉክክሩ በሚያይልባቸው ግዛቶች አሁንም ቢሆን ትራምፕ ክስ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡

እስካሁን በሁሉም ግዛቶች በተካሄደው የድምጽ ቆጠራ ባይደን በ5 ነጥብ 9 ሚሊየን ብልጫ አላቸው ተብሏል፡፡

እንዲሁም የግዛቶቹን ውክልና በሚይዘውና ወሳኝ በሆነው ድምጽ ደግሞ ባይደን 306 ድምጽ ሲይዙ ትራምፕ 232 ድምጽ ነው ያገኙት፡፡

 

ምንጭ፡-ቢቢሲ

በአብርሃም ፈቀደ

Exit mobile version