አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአልጄሪያ የኢፌዴሪ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በአልጀርስ ተቀማጭ ከሆኑት የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ዦን ኦሩዋርክ ጋር በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
አምባሳደሩ በኢትዮጵያ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ስራዎችና የተገኙ ውጤቶችን፣ እየተካሄደ ያለውን የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ ስራዎችን በማንሳት ለዴሞክራሲ ማበብ የሕግ የበላይነት መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም ማንኛውም ሀገር ህግን የተላለፉ አካላት በሚኖሩ ጊዜ ህግን የማስከበር ስራ እንደሚሰራ ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስትም በትግራይ ክልል ሕግን ተላልፈው የመሸጉ የህወሓት ፀረ ለውጥ አካላትን በህግ ፊት ለማቅረብ የሚያካሂደው ዘመቻ መሆኑን አስረድተዋል።
መንግስት የጀመረውን ህግና ስርዓት የማስከበር እንቅስቃሴም አጥፊው ቡድን ላይ ያነጣጠረና የትግራይ ህዝብን የማይመለከት መሆኑንም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በህወሓት ግጭት ቀስቃሽነት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን በተመለከተም ወደ ተረጋጋ ሕይወት እንዲመለሱ መንግሥት አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት።
አምባሳደር ዦን ኦሩዋርክ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው፤ ግጭቱ የሰብዓዊ ቀውስ እንዳያስከትል ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
እንዲሁም መንግስት እየወሰደ ያለው ህግን የማስከበር ዘመቻ ባጠረ ጊዜ ሊቋጭ እንደሚገባም ነው አምባሳደር ዦን ኦሩዋርክ የገለጹት።
ኤምባሲው የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከቱ መረጃዎች ሚሲዮኑ ለሚሸፍናቸው የአልጄሪያ፣ የቻድ እንዲሁም የኒጀር የመንግሥት አካላትና ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች በተከታታይ እንዲደርሳቸው እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ለአልጄሪያ የመገናኛ ብዙኀንም ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
አል-ፈጅር የተባለው ዕለታዊ የዓረብኛ ጋዜጣ በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ከአምባሳደር ነብያት ጋር ያደረገውን ቆይታ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል።