ዓለምአቀፋዊ ዜና

ባለፉት 10 አመታት ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በሶስት እጥፍ መጨመራቸው ተገለጸ

By Tibebu Kebede

December 30, 2019

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፈረንጆቹ 2010 ጀምሮ ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በሶስት እጥፍ መጨመራቸውን አስታወቀ።

ድርጅቱ ካለፉት አስር አመታት ወዲህ በህጻናት ላይ ከ170 ሺህ በላይ ከባድ የህግ ጥሰቶች መፈጸማቸውን አረጋግጫለሁም ብሏል።

ይህ ቁጥር ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ በጦር ቀጠና አካባቢ በሚገኙ ህጻናት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች ከሶስት እጥፍ በላይ መጨመራቸውን እና ሕጻናት የሚከፍሉት ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን ያሳያልም ነው ያለው ድርጅቱ።

እንደ ተመድ መረጃ በህጻናቱ ላይ ግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ ጾታዊ ጥቃት፣ ጠለፋ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ለጦርነትና ለተለያዩ የጉልበት ስራዎች ምልመላ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና የሚደርሱ ጉዳቶች ናቸው።

የተባበሩት መንግስታት በፈረንጆቹ 2018 ብቻ ከ24 ሺህ በላይ ጥቃቶች ህጻናት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ይፋ አድርጓል።

የዓለም አቀፉ የህጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሄነሪታ ፎር፥ በዓለም ዙሪያ የሚፈጠሩ ግጭቶች ረጅም ጊዜ እንደሚቆዩ ጠቅሰው የበርካታ ወጣቶችን ሕይወት ይቀጥፋሉ ብለዋል።

በጦርነት ተሳታፊ የሆኑ አካላት ከጦርነት ህጎች ዋነኛ የሆነውንና በጦርነት ወቅት ለህጻናት ጥበቃ ከለላ የሚሰጠውን ድንጋጌ በመጣሳቸው ሳቢያም በጦር ቀጠና የሚገኙ ህጻናት ሞት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ገልጸዋል።

አያይዘውም ከሚደርሰው የህጻናት ሞት አብዛኛው ይፋ እንደማይሆንም ጠቅሰዋል።

በ2019 በሶሪያ፣ የመን እና በአፍጋኒስታን የሚገኙ ህጻናት ለዚህ ጥቃት በልዩ ሁኔታ ተጋላጭ መሆናቸውን ዩኒሴፍ ገልጿል።

ተድርጅቱ በግጭጥት ተሳታፊ የሆኑ አካላት በህጻናት ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን እና የመሠረተ ልማት ውድመትን ለማስቆም እንዲሰሩም ጥሪውን አቅርቧል።

ምንጭ፦ አልጀዚራ