Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የ22ኛ ክፍለ ጦር አባላት ለህዳሴ ግድብና ለአካባቢው ደህንነት መረጋገጥ ተገቢውን ጥበቃ እያደረጉ እንደሚገኙ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሃገር መከላከያ ሰራዊት የምዕራብ ዕዝ 22ኛ ንስር ክፍለ ጦር አባላት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ እንደወትሮው በትጋት እየሰሩ መሆኑን አስታወቁ።

ከክፍለ ጦሩ አባላት መካከል ሌተናል ኮሎኔል ወንድሙ ሃብቴ እንደገለጹት፤ የ22ኛ ንስር ክፍለ ጦር አባላት አብዛኞቹ ለ21 ዓመታት በትግራይ ክልል የህዝብ ደጀን በመሆን ያገለገሉ ናቸው፡፡

“ሠራዊቱ የትግራይ ህዝብን ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ ሌት ተቀን በደሙ፣ በጉልበቱ፣ በገንዘቡ እና አቅሙ በፈቀደ ሁሉ መስዋዕትነት ከፍሏል” ነው ያሉት፡፡

ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ አባላት ላይ ያደረሰው ግፍ የተሞላበት ጭፍጨፋ ለሠራዊቱ ፈጽሞ የማይመጥን፣ አረመኔያዊ እና የሚወገዝ ድርጊት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የአብዛኛው የሰሜን ዕዝ ክፍለ ጦር አባላት በቅርቡ ለተጨማሪ ሃገራዊ ግዳጅ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንደተዛወሩ ገልጸው፤ ለህዝብ ክብር የተሰው ጓዶቻቸውን በማሰብ በቁጭት እየሠሩ መሆኑን ሌተናል ከሎኔል ወንድሙ አስረድተዋል፡፡

የክፍለ ጦሩ አባል ምክትል አስር አለቃ ገነት ቢቂላ በበኩላቸው “በሃገራችን ሠላም ሲያሳጣ የኖረውን የህወሓት ጁንታ ለህግ እንዲቀርብ የጀመርነውን ዘመቻ በስኬት እንወጣለን” ብለዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ የጁንታውን ህወሓት አባላት አጋልጦ በመስጠት ለሠራዊቱ ያለውን አጋርነት እንዲያሳይም ጠይቀዋል።

የህዳሴው ግድብ ከፍጻሜ እስከሚደርስ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ “በፕሮጀክቱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚነሳ የትኛውንም ሃይል አንታገስም” ነው ያሉት።

“የሰሜን ዕዝ አባሎቻችን መስዋዕትነት የፈጠረብን ቁጭት ተጨማሪ ወኔ እና ጉልበት ሆኖናል” ያለው ሻምበል ሄኖክ ተክለማርያም፤ የጁንታው ተላላኪዎች በመተከል ዞን የግድቡን አካባቢ ለማወክ የሚያደርጉትን ጥረት ለማክሸፍ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጿል።

በምዕራብ ዕዝ የ22ኛ ንስር ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ነገሪ ቶሊና ህብረተሰቡ ለሠራዊቱ ያሳየው ክብር ለበለጠ ሃላፊነት እንዳነሳሳቸው አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም “በሠራዊቱ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ውስጣዊ አንድነታችንን ለማፈራረስ በተነሱ ቡድኖች የተጠነሰሰ ሴራ ነው” ያሉት ብርጋዴር ጀኔራል ነገሪ፤ ሠራዊቱ ህዝባዊ ወገንተኝትን ያነገበ በመሆኑ ሴራው መክሸፉን ገልጸዋል፡፡

“የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ህዝብ ህልውና እንደሆነ ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ከምንጊዜውም በላይ ለዓለም አጉልቶ ያሳየ ነው” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በጁንታው ተልዕኮ በህዳሴ ግድብ አካባቢው ሁከት ለመፍጠር የሚደረግ ተደጋጋሚ ሙከራ እንዳለ የሚገልጹት አዛዡ፤ ከውስጥም ሆነ ከውጪ ሊቃጡ ለሚችሉ ማናቸውም የጥፋት ድርጊቶች አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ሰራዊቱ በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

Exit mobile version