Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሃን የአየር ሰዓት ድልድል ለማውጣት ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን እና ዓላማቸውን በመገናኛ ብዙሃን ለህዝቡ እንዲያስተዋውቁ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአየር ሰዓት ድልድል ለማውጣት መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ገለፀ።

በኢትዮጵያ በጠቅላላ ሃገራዊ ምርጫ ወቅት የመገናኛ ብዙሃን የአየር ሰዓት ስርጭታቸውና ከህትመት ገፃቸው ለፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ያውላሉ።

በተያዘው ዓመት ለሚደረገው ጠቅላላ ምርጫም ለፖለቲካ ፓርቲዎች ከሰው ንክኪ በጸዳ መልኩ በሶፍትዌር የታገዘ የአየር ሰዓት ድልድል ለማድረግ መዘጋጀቱን ነው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የገለፀው።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ የአየር ሰዓት ድልድሉን ለማድረግ የምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመነጋገር የሚያቀርበውን ቀመር እየጠበቀ ነው።

ቀመሩ በየምርጫ ዘመኑ የሚቀያየርና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሚደረግ ንግግር የምርጫ ቦርድ ከስምምነት የተደረሰበትን የአየር ሰዓት ድልድል ቀመር ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ያሳውቃል።

በዚህም መሰረት ባለስልጣኑ የተሰጠውን ቀመር ወደ ተዘጋጀው ሶፍትዌር በማስገባት የአየር ሰዓት ድልድሉን የሚያደርግም ይሆናል።

በቅድመ ዝግጅቱ ላይም ከምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የሚያነሱት ዋና ዳሬክተሩ፥ ሁለቱ ተቋማት በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ የባለሙያዎች ቡድን ኮሚቴ መዋቀሩን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንም በምርጫ ዘገባ ላይ ለጋዜጠኞችና ለመገናኛ ብዙሃን የስራ ሃላፊዎች የተለያየ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

ሆኖም ግን አሁንም መገናኛ ብዙሃን አሰራሮቻቸው ስነ ምግባርን ጠብቀው በመስራት የተለየ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ነው የሚሉት ዶክተር ጌታቸው ድንቁ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አባል ወይዘሪት ብዙወርቅ ከተተ በበኩላቸው የሲቪክ ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መራጩን ህዝብ የሚያቅፍ የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂ እየተዘጋጀ መሆኑ ተናግረዋል።

በበላይ ተስፋዬ

Exit mobile version