አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኩረጃን ለማስቀረት የአማራ ክልል መምህራን ማኅበር፣ የተማሪ ወላጆች ማኅበርና የክልሉ ትምህርት ቢሮ በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን አስታወቁ።
የአማራ ክልል መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት እናውጋው ደርሰህ፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአሳሳቢ ደረጃ እየተስፋፋ ላለው ኩረጃ ፈጣንና ዘላቂ መፍትሔ ካልተፈለገለት ኢትዮጵያን ለውድቀት ያጋልጣል ብለዋል።
ሀገሪቱ ብቁ የሰው ኃይል እንዳታዘጋጅ በማድረግ ኢትዮጵያን ከሌሎች ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ እንዳትሆን አቅም እንደሚያሳጣትም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሙላው አበበ በበኩላቸው፥ ኩረጃን የሚያበረታቱ የተማሪ ወላጆች እና “የትምህርት ቤታችን ገጽታ እንዳይበላሽ” በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ኩረጃ ሲከናወን በዝምታ የሚያልፉ መምህራን መኖራቸው በግምገማ መረጋገጡን ገልጸዋል።
ኩረጃን ለመከላከል ለተከታታይ ዓመታት ቢሠራም ውጤታማ ሊሆን አለመቻሉንና በኩረጃ ሂደት ተሳትፎ ያላቸውን ተማሪዎች፣ ፈታኞች፣ ሱፐርቫይዘሮችና ጣቢያ ኃላፊዎች ተጠያቂ የሚያደርግ የአፈታተን እና አስተዳደር መመሪያ ቢኖርም ትግበራው ክፍተት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ለኩረጃ መስፋፋት መንግሥት፣ መምህራን፣ ተማሪዎች እና የተማሪ ወላጆች ለትምህርት የሰጡት ትኩረት አናሳ መሆን፣ የፈተና ሥርዓትን አለማክበር፤ የመምህራን ተማሪ የማብቃት አቅም አናሳ መሆን እና የተማሪዎች በራስ የመተማመን አቅም ማጣት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
እነዚህን ችግሮች በፍጥነትና በዘላቂነት ለመፍታትእና በጥምረት ኩረጃን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር በትኩረት የተሰራ መሆኑን ከአማራ መገናኛ ብዙሃን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።