Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ቋሚ ኮሚቴው በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የኮቪድ 19 ማዕከላትን ጎበኘ

አዲስ አበባ ፣ህዳር 9 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የኮቪድ 19 ማዕከላትን ጎብኝቷል።

ቋሚ ኮሚቴው በቅዱስ ጴጥሮስ ሰፔሻላይዝድ ሆስፒታልና በጉለሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ 4 እና 2 በመገኘት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትና የህብረተሰቡ አጠቃቀም ምን እንደሚመስል ከተቋማቱ አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ህዝቡን ለማገልገል፣ ሆስፒታሉን ለማዘመንና አገልግሎቱን ለማሳደግ እየሰራ ያለው የስራ ተነሳሽት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን ቋሚ ኮሚቴው ባካሄደው የመስክ ምልከታ ተናግሯል፡፡

ከዚህ ባለፈም የተለያዩ ኮሚቴዎችን አዋቅሮ በሆስፒታሉ ውስጥ የኮቪድ 19 መከላከያ አልኮል እያመረተ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ሚናውን እየተወጣ  እንደሚገኝ ቋሚ ኮሚቴው ጠቁሞ ÷ ለሌላው ተሞክሮ ሊሆን ይገባልም ነው ያለው።

በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስር የሚገኘው የቦሌ ቡልቡላ የህክምና ማዕከል የመብራት ችግር ያለበት በመሆኑ በጀኔሬተር ቢገለገሉም በየጊዜው እየተበላሸ  ለከፍተኛ ወጪ መዳረጋቸውን  የሆስፒታሉ ስራ አስኪጅ ዶክተር ታምሩ አሰፋ ተናግረዋል፡፡

የኮቪድ 19 ህክምና ለመከታተል የሚያስችሉ ማሽኖች፣ የድንገተኛ መድሃኒት፣ የቬንተሌተርና የቁሳቁስ እጥረት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

አሁን ካለው የገበያ ሁኔታ አንጻር አብሮ ስለማይሄድ የበጀት ክለሳ የሚደረግበት ሁኔታ በማመቻት ቋሚ ኮሚቴው ከሚመለከተው አካት ጋር በመወያየት እገዛ ሊያደርግ ይገባል ማለታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version