አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቤቶች ሕዳር 7 ቀን 2013 ዓ.ም ተከፍተው የመማር ማስተማር ስራ እንደሚጀመር የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ አስታውቀዋል።
ዶክተር ቶላ በሪሶ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ በኮቪድ 19 ምክንያት በክልሉ ትምህርት ቤቶች ዝግ ሆነው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም የተነሳ በክልሉ ብቻ ከ6 ሚሊየን በላይ ልጆች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው መቆየታቸውንም ነው ያስታወሱት፡፡
በአሁኑ ወቅትም የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታን ከግምት ባስገባ መልኩ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን በማንሳት፥ ለዚህም ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ መገባቱን ገልፀዋል።
እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴም በክልሉ ለሚገኙ ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ መምህራን ስልጠና መሰጠቱንም ዶክተር ቶላ በሪሶ ተናግረዋል።
እንዲሁም በክልሉ ከ34 ሺህ በላይ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች እና ከ5 ሺህ በላይ ቤተ መፅሃፍት በህብረተሰቡ ተሳትፎ መገንባታቸውንም አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ህፃናት እንዳልተመዘገቡ የገለፁት ኃላፊው፥ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ እንዲያስመዘግቡም ጠይቀዋል።
የ8ኛ እና 12 ክፍል ተማሪዎች ትምህርት ቀደም ብለው መጀመራቸው የሚታወስ ነው፡፡