አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የተከዜ ሀይል ማመንጫ ግድብ በቦምብ ተደብድቧል ተብሎ በህወሓት አመራሮች የተሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ ባወጣው መግለጫ ተከዜ ግድብ እንደ ሌሎቹ ግድቦች በፌደራል መንግስት እንደሚተዳደር በመግለፅ የፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ከአምስት ቀን በፊት በስፍራው የነበሩ የፌደራል ፖሊሶች ላይ ጥቃት መፈፀሙን ገልጿል።
በፌደራል ፖሊሶቹ ላይ በተፈፀመው ጥቃት ምን ያህሉ ህይወታቸው እንዳለፈ እና እንደቆሰሉ ባይታወቅም 11 የፌደራል ፖሊሶች የ14 ሰዓት የእግር ጉዞ በማድረግ ጎንደር ከተማ መግባታቸውን አስታውሷል።
ነገር ግን በፌደራል ፖሊስ አባላቱ ላይ ጥቃት ከተፈፀመ በኋላ የፅንፈኛው ህወሓት ቡድን አክቲቪስቶች የተከዜ ግድብን መቆጣጠራቸውን ሲገልፁ ቆይተዋል ነው ያለው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ ባለሁለት ክበብ ቅስት ያለው እና በውሀ የተሞላ ግድብ በቦምብ ቢመታ ሊያስከትል የሚችለው መጥለቅለቅ እና ጥፋት ማንም ሊገምተው የሚችል መሆኑ የመረጃውን ሀሰተኛነት በቀላሉ ለማረጋገጥ ይቻላል ብሏል።
ተፈጥሯዊ ባህሪው ነውና፣ በህወሓት ውስጥ የሚገኘው የጽንፈኞች ቡድን በሀሰት ለማሳመን ጥረት ማድረጉን ይቀጥላል።
ህወሓት የሀሰት መረጃ የማሠራጨት ዘመቻውን በትጋት መቀጠሉን ሁሉም ሰው እንዲገነዘብም ጥሪ አቅርቧል።