አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በናይል ተፋሰስ የኢኳቶሪያል ሃይቆች ሃገራት የሚንስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሆነው ተመረጡ።
28ኛው የናይል ተሰፋሰስ ሃገራት የሚንስትሮች ምክር ቤት እንዲሁም 23ኛው በናይል ተፋሰስ የኢኳቶሪያል ሃይቆች ሀገራት የሚንስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ዓመታዊ ጉባኤ በዌቢናር በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባዔው ኢትዮጵያን ጨምሮ የቡሩንዲ፣ የዴሞክራቲክ ሪፐበሊክ ኮንጎ፣ ሱዳን፣ ግብፅ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እንዲሁም የኡጋንዳና ታንዛኒያ የውሃ ሚንስትሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
በዚህ ጉባዔ ላይ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በናይል ተፋሰስ የኢኳቶሪያል ሃይቆች ሃገራት የሚንስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡ ሲሆን፥ ለሚቀጥለው አንድ ዓመት ሰብሳቢ ሆነው የሚያገለግሉ መሆኑን ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚንስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በተመሳሳይ ጉባኤው የሩዋዳ የአከባቢ ጥበቃ ሚንስትር ዶክተር ጂያን ዲአርክ ሙጃዋማሪያን የናይል ተሰፋሰስ ሃገራት የሚንስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ አድርጎ መርጧል።
የዌቢናር ስብሰባው በመቀጠልም በሚቀጥለው አንድ ዓመት የኢኒሼቲቩን የአሰራር ሂደት፣
ሃገራቱ በተፋሰሱ በጋራ የሚሰሯቸውን የውሃ መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም የዓመቱን የበጀት አሰባሰብና አጠቃቀም ውይይት ተደርጓል።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ውይይት፥ የናይል ተፋሰስ ሃገራት በውሃ መሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስት የማድረግ ጉዳይ አጣዳፊ በመሆኑ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።
“በውሃ መሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ካልቻልን ስለሀገራቶቻችን የውሃ፣ የምግብ እና የኢነርጂ ደህንነት በሀቀኝነት መነጋገር አንችልም” ብለዋል።
ከሁሉ ይልቅ ደግሞ የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በተፋሰስ አባል ሀገራቱ ለሚኖረው ፍትሃዊ የውሃ የሃብት ክፍፍል በእጀጉ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።
ዘላቂ የናይል ተፋሰስ ሀገራትን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማስፈንና በውሃ አጠቃቀሙ ላይ ያለውን የቅኝ አገዛዝ ፍላጎት ያነገበውን ቅርስ ሆኖም የቀጠለውን እሳቤ ለማስተካል የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ማበጀት አስተማኝ መንገድ እንደሆን ገልጸዋል።
ይኸው ማእቀፍ ወደ ሥራ ቢገባ የሀገራት ሉዓላዊነትነትና እኩልነት የሚያከብርና የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያጎናፅፍ የትብብር ዘዴ ያስቀምጣልም ያሉት ሚንስትሩ፥ “ማእቀፉን ወደ ስራ የምናስገባበት ጊዜ አሁን ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለኢኒሼቲቩ አባል ሀገራቱ በየአመቱ የሚጠበቅባችውን መዋጮ በአግባቡ ሊያዋጡ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
ጉባኤው የኢኒሼቲቩ የ2020 አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦለት ውይይት ያደረገ ሲሆን፥ ኢኒሼቲቩ ያስቀመጣቸውን ግቦች ለማሳካት የሃገራቱ ቆራጥነት ማነስ፣ የግብፅ ተሳታፊ ያለመሆን፣ ከአለም አቀፍ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ የማግኘት እድል መቀነስ እንዲሁም በየሀገራቱ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ መቀያየር እንደ ችግር የተገለጹ ጉዳች ናቸው።