አዲስ አበባ ፣ ህዳር 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) 25ተኛ አመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ከንውኖች እያከበረ የሚገኝው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በነገው እለት ሶስተኛውን የውይይት መድረክ ያከናውናል።
ውይይቱ “ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ እና ለሀሳብ ብዝሀነት የሚዲያዎች ሚና” በሚል ርዕስ እንደሚደረግ የተቋሙ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰጠኝ እንግዳው ተናግረዋል።
በመድረኩ በግጭት ወቅት የሚዲያዎች ሚና ምን መምሰል እንደሚኖርበት ምክክር እንደሚደረግም ነው አቶ ሰጠኝ ያነሱት።
በፕሮግራሙ ላይ የዴሞክራሲ ተቋማት የተለያየ ዘርፍ ምሁራን እና የሚዲያ ባለሙያዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እያከበረ የሚገኘውን 25ኛ አመት በአል አስመልክቶ ከዚህ ቀደም ባለፉት 25 አመታት በሀገረ መንግስት ግንባታ የሚዲያው ሚና እና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የሚዲያ ተደራሸነት እና ስርጭት ዙሪያ ያተኮሩ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀቱ የሚታወስ ነው።
በዳዊት በሪሁን