አዲስ አበባ ፣ ህዳር 1 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጽንፈኛው ህወሓት ቡድን በሃገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈጸም ለድርድር የማይቀርብ ቀይ መስመር ጥሷል ሲሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
የሃገር ሉዓላዊ መገለጫ በሆነው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም ቀይ መስመር በጣሰው የህወሓት ቡድን ላይ የሚወሰደው ህግን የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ቃል አቀባዩ በትግራይ ክልል በህወሓት ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን ህግን የማስከበር እርምጃ አስመልክቶ ዛሬ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ገለጻ አድርገዋል።
በገለጻቸውም ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ባለፉት ሁለት አመታት ህገ-መንግስቱን የሚጻረሩ በርካታ ህገ-ወጥ ድርጊቶች ሲፈጽም መቆየቱን አስታውሰዋል።
በቅርቡም በሃገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈጸም ለድርድር የማይቀርብ ቀይ መስመርን መጣሱን ገልጸዋል።
በመሆኑም ቡድኑን ለህግ ለማቅረብ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።