Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ምክትል ርዕሰ መሰተዳድር አቶ ርስቱ ከስልጤ ዞን ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መሰተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ከስልጤ ዞን ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይቱ ወቅት የፌደራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ነዋሪዎቹ የተጀመሩ የመጠጥ ውሀና መስኖ ፣የመንገድ ፕሮጀክቶች አለመጠናቀቃቸውና የኤሌክሪክ ኃይል አቅርቦትና ተደራሽነት ተግዳሮት እንደሆነባቸው በውይይቱ ወቅት አንስተዋል ፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ አጋጥመው የነበሩ የጸጥታ ችግሮችና የመዋቅር ጥያቄን ለመመለስ በተደረገ ጥረት የበጀት እጥረት በማጋጠሙ በክልሉ መንግስት ሊሰሩ የታቀዱ መሰረተ ልማቶች በታሰበላቸው ልክ ማከናወን እንዳልተቻለ ገልፀዋል፡፡

የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እንደሚነሱ ጠቁመው አዳዲስ ስራዎችን ከማቀድ ይልቅ በፌዴራል ድጋፍ የሚሰሩና በጅምር የቀሩ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ የክልሉ መንግስት ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ብለዋል፡፡

ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በተያየዘ በዞኑ እራሱን የቻለ ማከፋፈያ እሰኪሰራ የቡኢን ማከፋፈያ በአማራጭነት መጠቀም እና በወራቤ ዩኒቨርሲቲ በኩል ያለውን የሀይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት ተቋሙ የሶላር ቴክኖሊጂን በግንባታ ጣሪዎቹ ላይ መጠቀም ጊዜያዊ መፍትሔ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴና መሰል ጉዳዮችን በኃላፊነት እንዲከታተል ከክልሉ ውሀ ቢሮ ኃላፊና ከስልጢ ዞን አስተዳደር ጋር የሚሰራ ቡድን በማዋቀር እንዲከታተል ይደረጋል ብለዋል፡፡

በዞኑ ተጀምሮ ያልተጠናቀቀው የዳሎቻ ካሊድ የመስኖ ፕሮጀክት 268 ሄክታር መሬት እንዲያለማ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ይህ ተሸሽሎ አስከ 10 ሺህ 80 ሄክታር መሬት ማልማት እንዲችል ጥናቱ ተጠናቆ በቅርቡ ስራው እንደሚጀመርም በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

በዩር አፕ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ መንገዶች ህብረተሰቡን ለጎርፍና መሰል ችግሮች ምክንያት መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን የበጀት ችግር ለመስተጓጎሉ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

የወራቤ ቦዠባር መንገድ ስራ በይፋ የተጀመረ ሲሆን የቆሼ ፣ጦራ ፣ሚቶ ፣ወራቤ መንገድ በቀጣይነት እንደሚሰራ የተጠቆመ ሲሆን የሁልባረግ ሀላባና ወደ አዲስ አበባ የሚወስደውም መንገድ አነስተኛ ጥገና እንደሚደረግለት መገለፁን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

Exit mobile version