አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ህዝብ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰበ፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ በህወሓት የጥፋት ቡድን የተቃጣውን አደጋ ለመመከት በሚደረገው ጥረት የክልሉ ህዝብ ከጠጥታ መዋቅሩ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት ስልጣኑን የተነጠቀው የህወኃት ቡድን እንደገና ለመመለስ ጦርነት መክፈቱ አሳፋሪ ነው ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡
ለሀገር ሰላም ዘብ በቆመው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት ማድረሱ የሚወገዝ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል የጸጥታ መዋቅርም ከሌሎች አጋር የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የሕዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ እየሠራ እንደሚገኝ ነው ኮሚሽነሩ ያስረዱት፡፡
የፌዴራል መንግሰትም አቋም ወስዶ ህጋዊ እርምጃ መጀመሩን ያነሱት ኮሚሽነሩ፤ የትግራይ ህዝብም ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በመሆን ሕወኃትን ሊታገል እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡