የሀገር ውስጥ ዜና

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ

By Abrham Fekede

November 04, 2020

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 25፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ፡፡

የኢፌዴሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው 21ኛ አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ መንግሥት የሀገርን ሰላምና ሕልውና፣ የሕዝብንና የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ እና ሀገሪቷን ወደ ሁከትና ብጥብጥ የሚወስዱ ማናቸውንም ድርጊቶችን የመከላከል ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብ፤ እንዲሁም በትግራይ ብሔራዊ ክልል ውስጥ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲሁም የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥሉ በተለይም የሀገርን ሉዐላዊነት የሚገዳደሩ፣ የፌደራል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በክልሉ እንዳይወጣ እና ሀገሪቷን የጦር አውድማ የሚያደርጉ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎችን ጭምር በመጣስ በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራት እየተፈፀሙ በመሆኑ፤ ይህን ሁኔታ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን በመረዳት፤ በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ልዩ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ እና ተግባራዊ በማድረግ ሁኔታውን በመቆጣጠር በሀገሪቱ ሰላምና ሕልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ መከላከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ መሰረት የሚከተለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።