Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጠ/ሚ ዐቢይ ሕዝቡ የሕወሓትን ትንኮሳ በመመከት ሀገሩን ለማዳን ከመከላከያ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሕዝቡ የሕወሓትን ነውጠኛ ቡድን ትንኮሳ በመመከት ሀገሩን ለማዳን ከመከላከያ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት በማድረስ ሰሜን እዝን ለመዝረፍ ሙከራ ማድረጉን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ “በኢትዮጵያውያን ላይ ከሐዲ ኢትዮጵያውያን ውጊያ ከፍተዋል፤ ኢትዮጵያም ጡቷ ተነክሷል” ብለዋል።

መንግስትም ጉዳዩን ከሚገባው በላይ ታግሷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ህወሓት ለትግራይ ሕዝብ ባያስብለትም መንግስት እንደሚያስብለት አንስተዋል፤ የትግራይ ሕዝብ ለህወሓት ምሽግ ለመንግስት ግን ወገን ነው ብለዋል በመግለጫቸው።

በዚህ የተነሣ መንግስት ሕዝብ እንዳይጎዳ ሲባል ከወሰን አልፎ መታገሱን በማውሳትም ትእግሥት በአንድ አቅጣጫ ብቻ ውጤት እንደማያመጣም አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ዘግናኝ ጥቃቶች መፈጸማቸውን አስታውሰው፥ ጥቃቶቹን የሕወሓት ነውጠኛው ቡድን እንዳቀናበራቸውም ነው የገለጹት።

ህወሓት መቐለ ባለው ጦር ላይ ጥቃት በመሰንዘር መሣሪያ ለመዝረፍ እና ምሽግ ያለውን ጦር ለመምታት መሞከሩንም ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም በዳንሻ በኩል በአማራ ክልል ላይ ጦርነት ከፍቷልም ነው ያሉት።

ሕዝቡም የሕወሓትን ነውጠኛ ቡድን ትንኮሳ በመመከት ሀገሩን ለማዳን ከመከላከያ ጎን እንዲቆም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

Exit mobile version