አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ወለጋ ዞን አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው ሰላም እንዲረጋገጥ ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው እንደቀሚቀጥሉ ተገለፀ ።
በነቀምት ከተማ የዞን እና የወረዳ መስተዳድርና የፀጥታ አካላትን ጨምሮ ከምዕራብ ዕዝና ከፌደራል ፖሊስ የተውጣጡ አመራሮች በጋራ መክረዋል።
ወይይቱን የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አስመራ ኢጃራ፣ የምዕራብ ዕዝ ኢንዶክትሪኔሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር እና የዞኑ የፀጥታ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኮለኔል ተስፋዬ ነጋሽ እንዲሁም የምዕራብ ኦሮሚያ ልዩ ሀይል አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ጋሊ ከማል መርተውታል፡፡
አቶ አስመራ ኢጃራ እንደገለፁት ኦነግ ሸኔ በዞኑ ብዙ ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
ኮለኔል ተስፋዬ ነጋሽ በበኩላቸው ሰራዊቱ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የፀረ ሰላም እንቅስቃሴ የሚታይባቸውን አካባቢዎች በመለየትና የተጠኑ የፀረ ሽምቅ ስምሪቶችን በማድረግ ውጤታማ ስራዎችን እየሰራ መምጣቱን ጠቁመዋል ።
ረዳት ኮሚሽነር ጋሊ ከማል ጥፋት የሚያደርሱ ቡድኖችን እስከነ ሴላቸው ተከታትሎ ከመደምሰስ ባሻገር የሚያገኛቸውን ድጋፎች በማቋረጥ የተሰራው ስራ ጥሩ እንደሆነ መናገራቸውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።