አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎችን አወገዘች፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ በሰጡት መግለጫ፥ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ፣ በደቡብ ክልል ቤንች ሼኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምንም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት የሌላቸው ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ አውግዘዋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ በዓመታዊ ስብሰባ ላይ እያለ ድርጊቱን የሰማው መሆኑን በመጥቀስ፥ ድርጊቱ ሲኖዶሱንና ቤተ ክርስቲያኗን በእጅጉ ያሳዘነ ኢ ሰብአዊ መሆኑን በመግለጽ አውግዘዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኗም አላስፈላጊ በሆነ ምክንያት በግፍ ለተገደሉና ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ልባዊ ሐዘኗን ትገልጻለች ነው ያሉት፡፡
መላው ኢትዮጵያውያንም እንደ እግዚብሔር ሐሳብ ሁሉም የዚህ ዓለም እንግዶች መሆኑን በመገንዘብ በወንድማማችነት፣ በፍቅርና በአንድነት በመተሳሰብ እግዚአብሔር በሰጠው ምድር ላይ በፍቅር እንዲኖሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዳግሞ እንዲህ ዓይነት ኢ ሰብአዊ ድርጊት እንዳይፈጸምም መንግሥት ለዜጎች አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግና ወንጀለኞችንም ለፍርድ እንዲያቀርብም ጠይቀዋል፡፡
መላው ኢትዮጵያውያንም በቀጣይ ለጋራ ሰላምና አንድነት እንዲቆሙ ጥሪ መቅረቡንም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡