አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕድን እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በምዕራብ ወለጋ ዞን በዜጎች ላይ በደረሰውን ጥቃት ማዘናቸውን ገለፁ ፡፡
ኢንጂነር ታከለ ኡማ ጥቃቱን አስመልክተው በፌስቡክ ገፃቸው ላይ በኢትዮጵያውያን ወገኖች ላይ እየደረሰ የግፍ ግድያ እጅግ ያማል ሲሉ አስፍረዋል።
ንፁሃን ዜጎችን በዘርና በኃይማኖት ለይቶ በመግደል ለወገኑ እንደሚታገል የሚያስመስለው አካል ፀረ-ኢትዮጵያና የሰውነት ጠላት እንጂ የማንም ወገን ሊሆን አይችልም ነው ያሉት።
ሰውን በከበረ ዋጋው የማያይ፣ ራሳቸውን መከላከል ለማይችሉ ምስኪኖች የማይራራ ታጋይ ታጋይ አይደለም በማለትም ተናግረዋል።
እንደ ኢትዮጵያውያን ትግላችን መሆን ያለበት ለሕዝቦች እኩልነት እንጂ ለማንም ወገን የበላይነት ሊሆን አይገባም ያሉት ሚኒስትሩ ማንኛውንም ወገን ለይቶ በመጥላትና ነጥሎ በማጥቃት የሚደረግ እንቅስቃሴ ለየትኛውም ወገን መቆም የማይችል፣ ከመነሻው የተሸነፈ የሰውነት ጠላት ነው በማለት አንስተዋል፡፡
እየሆነ ያለው ሰው የሆነን ሁሉ ልብ የሚሰብር ነው፤የንፁሃኑ ደም ያለፍርድ በከንቱ ፈሶ አይቀርም ያሉ ሲሆን ላዘኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ሁሉ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው “ሰላማዊ ህዝብን በመጨፍጨፍና በማስጨፍጨፍ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ሰው የመሆን ስብዕና የጎደላቸው ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በማውገዝ የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀው ጥቃቱን ባደረሱ አካላት ላይ መንግስት የማያዳግም እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
‘’በዜጎች ላይ የደረሰው አሰቃቂ ጥቃት እጅጉን የሚያሳዝንና ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ ነው” ብለዋል፡፡
ጥቃቱ ፍፁም ሰላማዊ በሆኑ ንፁሃን ዜጎች ላይ የተቃጣ መሆኑ አጥፊ ቡድኑ የሚከተለው መንገድ ኋላ ቀርና ጭካኔ የተሞላበት መሆኑን እንደሚያመላክት ጠቅሰዋል።
ቡድኖቹ የፈጸሙት አፀያፊ ድርጊት የኢትዮጵያውያንን አንድነትና ወንድማማችነት ሊቀይረው እንደማይችል ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የጥፋት ሃይሎችን በጋራ በመዋጋት የሀገሪቱ የዜጎች ደህንነት የተረጋገጠባት እንድትሆን ሁሉም በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡
እንደ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት የ32 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡