አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 21 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያ የከንቲባዎች ፎረም የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ተመረጡ፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር “የተሸለ ከተማ ለተሻለ ህይወት” በሚል መሪ ቃል በሃገር አቀፍ ደረጃ ከንቲባዎች በቋሚነት ተገናኝተው ስለከተሞች ጉዳይ የሚመካከሩበት፣ የዕርስ በርስ ትስስር የሚፈጥሩበት፣ በችግሮች ዙሪያ በጋራ መፍትሄ የሚፈልጉበት መድረክ ለማመቻቸት በአዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያ ከንቲባዎች ፎረም ተመስርቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያ የከንቲባዎች ፎረም ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡ ሲሆን ሰባት አባላት ያሉት የቦርዱ ሥራ አስፈጻሚዎችም ተሰይመዋል፡፡
በዚሁ መሠረት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ (የቦርዱ ሰብሳቢ)፣ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬን የሐዋሳ ከተማ አስተዳዳር ምክትል ከንቲባ (ምክትል ሰብሳቢ) እንዲሁም ዶክተር ድረስ ሣህሉ የባህዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ (ጸሐፊ) ሆነው ተመርጠዋል፡፡
የአዳማ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ፣ የአሶሳ፣ የድሬዳዋ እና ደገሀቡር ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች የቦርዱ አባላት ሆነዋል።
የቦርዱ የስራ ዘመን ሁለት ዓመት መሆኑንም ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡