አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ የሚገኙ አምስት የሪል ስቴት አልሚ ኩባንያዎች ለ”ገበታ ለሀገር” የ25 ሚሊየን ብር የእራት ኩፖን ገዙ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ተግባራዊ ላደረጉት ኮይሻ፣ ጎርጎራ እና ወንጪ የመስህብ ስፍራዎች መገንቢያ ”ገበታ ለሀገር” የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ግብዣ መርሐ ግብር በመሰናዳት ላይ ይገኛል፡፡
ለእነዚህ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ እንዲሆንም በአዲስ አበባ የሚገኙት አያት ሪል ስቴት፣ ዮሲ ሪል ስቴት፣ ይርጋለም ሪል ስቴት፣ ፀሐይ ሪል ስቴት እና ካራቆሬ ሪል ስቴት በእራት ግብዣው ለመሳተፍ እያንዳንዳቸው የ5 ሚሊየን ብር ኩፖን ገዝተዋል፡፡
የሪል ስቴት አልሚ ኩባንያዎቹ ላደረጉት አስተዋጽኦ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዲኤታው አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ምስጋና አቅርበዋል።
ሌሎች መሰል አካላት ይህንን አርአያ በመከተል ለሀገር ልማት እና ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡