Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

84 ኢትዮጵያዊያን ከሱዳን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 16፣ 2012(ኤፍ ቢሲ) የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ 84 ኢትዮጵያዊያን ከሱዳን ወደ ሀገራቸው በዛሬው ዕለት ተመልሰዋል።

ኢትዮጵያውያኑ በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከዓለምአቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር በመተባበር ባከናወነው የቅንጅት ስራ ነው ወደ ሀገራቸው የተመለሱት።

ተመላሾቹ በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች አማካይነት በሱዳን በኩል ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለመሄድ ደላሎች ባዘጋጇቸው መጋዝኖች ተዘግቶባቸው የነበሩ ናቸው።

ኤምባሲውም ከሱዳን የሰዎች ሕገ-ወጥ ዝውውር ቁጥጥር መስሪያ ቤት ጋር በቅርበት በመስራት ከአደጋ በማዳን በካርቱም የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ማቆያ ማዕከል ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱ ነው የተገለጸው።

ተመላሾቹ በካርቱም የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ማቆያ ማዕከል በቆዩባቸው ጊዜያት ኮሚዩኒቲው የምግብ፣ ህክምና፣ ንጽህናና ምክር አገልግሎትና እንክብካቤ ሲደረግላቸው የነበረ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከዚህ ቀደም ከ300 በላይ የሚሆኑ የህገወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ እና በእስር ላይ የነበሩ ዜጎቻችንን ከሚመለከታቸው የሱዳን ባለሥልጣን መስሪያ ቤቶችና የተለያዩ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበርና በቅርበት በመስራት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ ይታወሳል።

Exit mobile version