Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ስፖርት ኮሚሽን  በአፋር ክልል በጎርፍ ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 19 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን በአፋር ክልል በጎርፍ ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች  2ነጥብ 6  ሚሊየን ብር ግምት ያላቸዉ የተለያዩ ቁሳቁሶችና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

ኮሚሽኑ ድጋፉን ያደረገው ከተጠሪ ስፖርት ተቋማትና  ከሀገር አቀፍ ስፖርት ማህበራት  ጋር በጋራ  መሆኑም ተገልጿል።

ከድጋፍ አሰጣጥ ፕሮግራም በመቀጠል የችግኝ ተከላ እና የስፖርት ልማት እንቅስቃሴዎች ተጎብኝተዋል።

አቶ መሀመድ ሐሰን የአፋር ክልል የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኋላፊ÷ ሰብዓዊነት ተሰምቷችሁ በእኔነት ወደ ክልሉ በመምጣታችሁ እናመሰግናለን ብለዋል።

አቶ ኤሊያስ ሽኩር የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሸን ኮሚሽነርበወቅቱም ÷ ኮሚሽኑ የስፖርት ቤተሰቡን በማስተባበር የሰብአዊ ድጋፍ ስራዎችን ከዚህ ቀደምም  ሲያከናወን መቆየቱን አንስተዋል።

በአፋር ክልል በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የደረሰው የጎርፍ አደጋን ተከትሎም ኮሚሽኑ የአቅሙን ከመደገፍ ባለፈ ወደ ክልሉ በመሄድ የስፖርት እንቅስቃሴ ላይ አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል ።

አቶ ዱቤ ጅሎ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ÷አፋር ክልል ላይ በአጫጭር የሩጫ እና በዉርወራ ስፖርት ላይ መስራት ክልሉን እና ሀገርን ዉጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

አቶ ዱቤ አያይዘውም የክልሉ ሞቃታማ አየር ሁኔታ ለብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ምቹ ስለሚሆን ከክልሉ ጋር ተቀራርቦ መስራት ጠቃሚ  ነው ብለዋል።

ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው÷  ቀደም ሲል ከሰጡት ገንዘብ በተጨማሪ 600 ሺህ ብር በኦሊምፒክ ኮሚቴ በኩል ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የቶኪዮ 2020 ዝግጅት ኮሚቴ አባል ሲሆኑ ስፖርት ለሀገር ገፅታ ግንባታ ትልቅ መሳሪያ በመሆኑ ክልሉ የጀመራቸዉ የልማት ስራዎች ተጠናክረዉ ይቀጥላሉ ብለዋል።

አቶ አህመድ ኢብራሂም የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኋላፊም ለተደረገዉን ድጋፍ  ማመስገናቸውን ከስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

 

Exit mobile version