አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሽከርካሪ ፍቃድ ሰጪ ተቋማት እና የተሸከርካሪ ምርመራ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደረገ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደረገ።
የትራንስፖርት ዘርፍ የሀገሪቱን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማሳደግ ረገድ ጉልህ ድርሻ አለው፡፡
በዘርፉ ከሚስተዋሉ በርካታ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው በአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጥ እና ፍቃድ አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ መመሪያዎችን መሰረት በማድረግ በናሙና በተመረጡ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት፣ ብቃት አረጋጋጭ እና ፍቃድ ሰጪ ተቋማት ላይ ጥናት ተካሂዷል፡፡
መድረኩ በዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት፣ የአፈፃፀም ክፍተቶችን ለማረም እና በጥናቱ ላይ ውይይት ተደርጎ የመፍትሄ ሃሳብ ለማስቀመጥ በማለም የተዘጋጀ ነው፡፡
የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ምትኩ አስማረ በሀገሪቱ በትራፊክ አደጋ ምክንያት በሰው ህይወት መጥፋት እና ንብረት ውድመት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በቀጣይ ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ ሁሉም ሀላፊነት መወጣት አለበት ብለዋል፡፡