አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአሜሪካ በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከ225 ሺህ አለፈ፡፡
በቫይረሱ ከተጠቁ ሃገራት መካከል ዋነኛዋ በሆነችው አሜሪካ 8 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎች በኮቪድ መያዛቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ከ8 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎች ውስጥ ከ3 ሚሊየን 422 ሺህ በላይ ሰዎች ማገገማቸውን የጆንሆፕኪንስ መረጃ ያመላክታል፡፡
በአሜሪካ በአንድ ቀን በቫይረሱ የሚያዙት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል ተብሏል፡፡
አርብ እና ቅዳሜ ብቻ ከ83 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡
እሁድን ጨምሮ ለሰባት ተከታታይ ቀናት የተያዙ ሰዎች በአማካይ ከ68 ሺህ በላይ ሲሆኑ ይህ ቁጥርም በሐምሌ ከተመዘገበው የሚልቅ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአሜሪካ አሁንም ጥንቃቄዎች ካልተደረጉ የሟቾች ቁጥር እንደሚጨምር ባለሙያዎች እየገለጹ ነው፡፡
ባለሙያዎቹ 95 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ተገቢ በሆነ መንገድ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ቢጠቀም የ100 ሺህ ሰዎችን ህይወት መታደግ ይቻል እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ምንጭ፡-ሲ ኤን ኤን