Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጃፓን ከ2007 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ሃገር ዜጋን በሞት ቀጣች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጃፓን ከፈረንጆቹ 2007 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ሃገር ዜጋን በሞት መቅጣቷ ተነገረ።

የ40 ዓመቱ ቻይናዊ ዌይ ዌይ አራት የቤተሰብ አባላትን ህይወት ማጥፋቱን ተከትሎ ቶኪዮ በሞት መቅጣቷ ነው የተነገረው።

ቅጣቱ በሞት የተቀጡ ጥፋተኞች ስም ዝርዝር ይፋ መደረግ ከጀመረበት የፈረንጆቹ 2007 ወዲህ የመጀመሪያው በውጭ ዜጋ ላይ የተፈጸመ መሆኑን የሀገሪቱ የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ዌይ በፈረንጆቹ 2003 አጋማሽ ላይ ሁለት የቻይና ዜግነት ካላቸው ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ግድያውን መፈጸሙን የሃገሪቱን ሚዲያዎች ዋቢ ያደረጉ ዘገባዎች አመላክተዋል።

ግብረ አበሮቹ ወደ ቻይና ሸሽተው እዚያው የተያዙ ሲሆን፥ አንደኛ በ2005 በሞት ሲቀጣ ሌላኛው ደግሞ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

ጃፓን ከባድ ወንጀል ፈጽመዋል ባለቻቸው ግለሰቦች ላይ የሞት ፍርድን ተግባራዊ ከሚያደርጉ ሃገራት መካከል አንደኛዋ መሆኗ ይነገራል።

ሃገሪቱ ባለፈው ዓመት 15 ሰዎችን በሞት ስትቀጣ ወደ 120 የሚጠጉ እስረኞች ደግሞ ቅጣታቸውን እየተጠባበቁ ነው ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በፈረንጆቹ 2012 ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በሞት የተቀጡ ሰዎች ቁጥር 39 ደርሷል።

ምንጭ፡- አልጀዚራ

Exit mobile version