Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ፓርቲዎች በቅርበት አብረው እንዲሠሩ ለማስቻል ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው-ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረጉ ውይይቶች ፓርቲዎች በቅርበት አብረው እንዲሠሩ ለማስቻል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ።

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ በዛሬው እለት የምክክር መድረክ አካሂደዋል።

በውይይቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተሳታፊነት ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ውይይቱን አስመልክቶ በፌስቡክ ገፃቸው ባወጡት መረጃ፥ “የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ዛሬ በመቀጠሉ ደስ ብሎኛል” ብለዋል።

እነዚህ ውይይቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅርበት አብረው እንዲሠሩ፣ ለወቅታዊ ጉዳዮች የጋራ መፍትሔ እንዲያበጁ፣ እንዲሁም ለሀገራችን እና ለሕዝባችን የሚጠቅም የዕድገት እና የብልጽግና የጋራ ራእይን እንዲያዘጋጁ  ለማስቻል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዛሬው የምክክር መድረክ ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊነት በኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አደረጃጀት ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫና የማያግባቡን ታላላቅ አጀንዳዎች በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች የተወያዩት።

ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊነት በኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ፖለቲካ አደረጃጀት ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው በሚሉት አጀንዳዎች ላይ የመወያያ ጽሁፎች ቀርበዋል።

ፓርቲዎቹ ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊነት በኢትዮጵያ በሚል ባደረጉት ውይይት ወደ ኋላ በመመለስ ከህገ መንግስት በፊት ኢትዮጵያ ትተዳደርበት የነበረው ፍትሐ ነገስትን አንስተው መክረዋል።

እንዲሁም በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን ከፍትሐ ነገስት ወደ ህገመንግስት ሽግግር የተደረገበት ጊዜና የህገመንግስቱ ደካማና ጠንካራ ጎኖች በውይይቱ ተነስተዋል።

በ1983 ዓ.ም የተደረገውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ የመጣው ህገ መንግስትም ምን ዓይነት ጠንካራ ጎኖች ነበሩት በሚለው ላይ ትኩረት ማድረጋቸውም ተጠቅሷል።

በዚህም ህገ መንግስቱ ለብሄር ብሄረሰቦች ዕውቅና መስጠቱ፣ የስልጣን ገደብ ማበጀቱ እና ሌሎችም ተነስተውበታል።

ከዚህ ባለፈም ወደ ተግባር የመውረድ ችግር ነበረበት በሚል የነበረበት ውስንነት በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል።

እንዲሁም ነጻ የዴሞክራሲ ተቋማት ላይ ጣልቃ መግባት ከሚጠቀሱ ውስንነቶች መካከል መሆናቸውም ነው በመድረኩ የተነሳው።

በጥቅሉ ከ1931 እስከ 1983 ዓ.ም የነበሩት ህገ መንግስቶች የራሳቸው የሆነ መልካምና ውስንነቶች ነበሩባቸው ተብሏል።

እንደ ፍትሐ ነገስት፣ የገዳ ስርዓት እንዲሁም ሌሎች የሚጠቀሙባቸው ባህላዊ ስርዓቶች ያለማካተታቸው እንደችግር ተነስቷል።

የግለሰብ መብትን መሰረት ያለማድረጋቸው፣ የቅቡልነት ችግር፣ ህገ መንግስቱን በማፀደቁ ሂደት የነበረው የአሳታፊነት ጉድለት እንደ ችግር ተጠቅሰዋል።

Exit mobile version