የሀገር ውስጥ ዜና

አዲስ ወግ የውይይት መድረክ በሂልተን ሆቴል ተካሄደ

By Tibebu Kebede

December 25, 2019

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 15 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚዘጋጀው አዲስ ወግ የውይይት መድረክ በሂልተን ሆቴል ተካሄደ።

መድረኩ “የሚዲያው ሚና ሃሳቦችን ለማቀራረብ” በሚል መሪ ቃል ነው የተካሄደው።

በመድረኩ ላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካም ሆነ የማህበራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የሚንፀባረቁ ሃሳቦችን ለማቅረብ መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተገልጿል።

ለሀገሪቱ መፃኢ እጣ ፈንታ መደማመጥና የሃሳብ የበላይነት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን፥ በውይይቱ ላይ ሃሳቦችን በማቀራረብ ረገድ መገናኛ ብዙሃን የነበራቸውን ሚና በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ቀርቧል።

በተጨማሪም መገናኛ ብዙሃን የሃሳብ ብዝሃነትን ማስተናገድ ላይ ክፍተት እንደነበረባቸውም ተነስቷል።

ከማቀራረብ ይልቅ ግጭት ቀስቃሽ ዘገባዎችም በማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት ተሰራጭተዋልም ነው የተባለው።

ከዚህ ባለፈም በሚዲያ ባለሙያዎች ላይ አሁንም ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ተፅዕኖዎች መኖራቸው ነው የተገለጸው።

በዚህም ብሄር ተኮርና እነሱና እኛ የሚሉ መገናኛ ብዙሃን መፈጠራቸው የተነሳ ሲሆን፥ የሴቶች ተሳትፎና፣ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ መሆን ላይ ክፍተት መኖሩም ተጠቅሷል።

ሃሳቦችን በማቀራረብ ረገድ የመገናኛ ብዙሃንን ሚና በተመለከተም ከተወያዮቹ ሃሳብ ተሰጥቶበታል።

አዲስ ወግ የውይይት መድረክ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች መካሄዱ ይታወሳል።

በሃብታሙ ተክለስላሴ