ቴክ

ፌስ ቡክ መገበያያ መተግበሪያ ለኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ጀመረ

By Meseret Awoke

October 12, 2020

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የፌስ ቡክ ኩባንያ በፌስ ቡክ ገጹ አማካኝነት የሚሰራ ምርቶችን መሸጥ እና መግዛት የሚያስችል የፌስ ቡክ መገበያያ መተግበሪያ ለኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

የፌስ ቡክ የግብይት መድረኩ ኢትዮጵያውያን የሚፈልጓቸውን ምርቶች በቀላሉ በፌስ ቡክ ገጻቸው አማካኝነት መግዛት እና መሸጥ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያም አገልግሎቱ ከዚህ ወር መጨረሻ ጀምሮ ቀስ በቀስ ተደራሽ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፤ እስከ ሕዳር ወር መጨረሻ ድረስ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡

የአገልግሎቱን መጀመር አስመልክቶ የፌስ ቡክ የምስራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ የሕዝብ ፖሊሲ ዋና ኃላፊ ሜርሲ ንድግዋ ‘‘በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኤሌክትሮኒክ ግብይትን የሚያግዝ የፌስ ቡክ መገበያያ መድረክ በማስጀመራችን ደስታ ይሰማናል’’ ብለዋል::

የፌስ ቡክ ገጽን በመጠቀም ኢትዮጵያውያን የተወሰነ ግብይት እያከናወኑ እንደሆነ ስለምናውቅ የፌስ ቡክ ኩባንያም ደህንነቱ እና አስተማማኝነቱ የተጠበቀ አዲስ የግብይት መተግበሪያ ለኢትዮጵያውያን ማቅረቡ ትልቅ ስኬት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በግብይት መተግበሪያው ላይ ያለውን የግብይት መድረክ ቁልፉን በመጫን ወይም የፌስ ቡክ ግብይት ድረ ገጽን በመጎብኘት የሚፈልጉትን የዕቃ ዓይነት ከዝርዝሮቹ መሃል በዓይነትም ሆን በቦታ መምረጥ አልያም የሚፈልጉትን የምርት ዓይነት በቀጥታ ገብተው መጻፍ ይችላሉ፡፡

የግብይት ቁልፉን ሲጫኑ ተጨማሪ ዝርዝሮችን የሚያሳይ ሲሆን በሜሴንጀር አማካኝነት መልዕክቶችን ለሻጮች መተው ያስችላል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም የሻጩን አጭር ግለ ታሪክ በመጫን ስለ ሻጩ መረጃ ማግኘት እና የሽያጭ ደረጃ ድልድሉን ማየት የሚያስችል ሆኖ ግዢና ሻጮች ስለ ክፍያ እና ለሎች ዝርዝር ሁኔታውን መረጃ የሚለዋወጡበት መድረክ ነው፡፡

ስለግብይት መተግበሪያው አሰራር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከታች ያለውን ድረ-ገጽ መጎብኘት ይችላሉ፡፡

https://www.facebook.com/marketplace/learn-more/buying