አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ኬሚካል የሚረጩ 5 ተጨማሪ አውሮፕላኖችን እስከ መጪው እሮብ ድረስ ከውጭ ለማስገባት ጥረት እያደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የአንበጣ መንጋው በአሁኑ ወቅት በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መከሰቱን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስቴርም ከክልሎች ጋር ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር እና አስፈላጊውን የኬሚካል፣ የተሽከርካሪዎች፣ የአሰሳ ሄሊኮፕተሮችና የመርጫ አውሮፕላኖች እንዲሁም በቂ ባለሙያዎችን በመመደብ ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር ጭምር ቅንጅት በመፍጠር የመቆጣጠር ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ችግሩ እየሰፋ በመምጣቱ ተጨማሪ 5 አውሮፕላኖችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የአንበጣ መንጋው ወደ ሌሎች አካባቢዎች በስፋት እንዳይዛመት ለማድረግ የመከላከል ሥራውን በጥንቃቄ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በአንበጣው ጉዳት የደረሰባቸውን አርሶ አደሮች ለመደገፍ የመለየት ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።
የመከላከል ስራው ውጤታማ እንዲሆንም በተዋረድ ያሉ የመንግስት መዋቅሮች ህብረተሰቡን በሚፈለገው ደረጃ በማሳተፍ እና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር መስራት እንደሚገባቸው አንስተዋል።
ሚኒስትሩ የግል ባለሀብቱም በዚህ ፈታኝ ወቅት በሚችለው ሁሉ ከህዝቡና ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
በትዝታ ደሳለኝ