የሀገር ውስጥ ዜና

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በዘርፉ በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ነው

By Tibebu Kebede

December 24, 2019

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 14፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝ ቢሮ ሰላማዊ የጉብኝት ስርዓት ማስፈን በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ነው

በውይይት መድረኩ መንግስታዊ  ተቋማት ፣ አስጎብኝ ድርጅቶች ፣የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የሆቴል ባለቤቶች እና  የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ በውይይቱ ባድረጉት ንግግር፥ ክልሉ የበርካታ ቱሪስት መስህቦች መዳረሻ መሆኑን አውስተዋል።

ይሁን እንጅ የባህልና የቱሪዝ ዘርፍ  በርካታ ችግሮች የሚስተዋሉበት መሆኑን ነው ሃላፊው የተናገሩት።

ጠንካራ የማርኬቲንግ እና የትውውቅ ስራ አለመስራት፣ ቅርሶችን በወቅቱና በአግባቡ አለመጠገን እንዲሁም   ከፍተኛ የሆነ የቅርስ ዝውውር እና ስርቆት መስፋፋት  በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች  መሆናቸውን  አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም  የአካባቢውን ባህልና ወግ አለማክበር፣ የስነ-ምግባር መርሆችን ጠብቆ አገልግሎት አለመስጠትና በቱሪስት ላይ ወከባ መፈፀም ብሎም  የተጋነነ ክፍያ መጠየቅ በዘርፉ ለዘርፉ ዕድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮች ናቸው።

እንዲሁም የመሠረተ ልማት ችግር እና ሀገር በቀል የግንባታ ጥገና እውቀት አለመኖር  እና የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ያለ ስራ ፍቃድ  ወደስራ  መግባት  ችግሮች መኖራቸውን ተናግርዋል።

ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ ደባርቅ፣ ደሴ፣ ደብረ ብርሃን እና ደብረ ታቦር የክልሉ ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር ሙሉቀን፥ በተያዘው ዓመት በምስራቅ አማራ ተጨማሪ የመስህብ መዳረሻዎችን ለማካተት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ሰላማዊ የጉብኝት ስርዓትን ለማስፋት እና ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ በሚስተዋሉ  ችግሮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረው ውይይት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም  ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት 11 ሚሊየን 666 ሺህ 624 የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገር ቱርስቶች ክልሉን  የጎበኙ ሲሆን ፥ በዚህም 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን አንስተዋል።

በተያዘው ዓመት ደግም 65ሚሊየን ብር የቅርስ ጥገና ስራ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቱሪዝም ዘርፉ ያሉትን ችግሮች በመፍታት ሠላማዊ ጉብኝትን ለማስፈን  እንደሚሰራ ተናግረዋል።

 

ናትናኤል ጥጋቡ