ስፓርት

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በ22 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ተሸጠ

By Tibebu Kebede

October 07, 2020

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት እና የውድድር ስያሜ ለዲ ኤስ ቲቪ በ22 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ተሸጠ።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የፕሪሚየር ሊግ ውድድሩን በቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ለማስተላለፍ ፍላጎት ያላቸውን ድርጅቶች ባወጣው ጨረታ መሠረት ሲያወዳድር መቆየቱ ተገልጿል፡፡

ከተወዳዳሪዎች መካከልም መልቲ ቾይዝ ኢትዮጵያ ባቀረበው ቴክኒካል እና የገንዘብ ፕሮፖዛል የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ በቀጣይ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን በዲ ኤስ ቲቪ ለማስተላለፍ ተመርጧል፡፡

ድርጅቱ ውድድሩን በቀጥታ ለማስተላለፍ እና ለውድድር ስያሜ ለአምስት ዓመት 22 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር አቅርቧል።

በተጨማሪም ለስልጠና እና አቅም ግንባታ፣ ለፕሮዳክሽን፣ ለአየር ሰዓት ወጪ እና ለአይ ሲቲ መሠረተ ልማት ግንባታ ከ45 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ እንደሚያደርግ ነው የተገለጸው፡፡

በአጠቃላይ በአምስት አመት ውስጥ ከ68 ሚሊየን ዶላር በላይ ፈሰስ እንደሚያደርግ በመግለጹ ማለቱ አሸናፊ መሆኑ ተጠቁሟል ፡፡

በተለይም ድርጅቱ የሀገሪቱን ስፖርት ደረጃ ለማሻሻል በታዳጊ ወጣቶች ላይ፣ የዳኞች እና አሠልጣኞች አቅም ግንባታ፣ ከስታዲየም አካባቢ ፀጥታ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ማሳወቁን ከስፓርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ድርጅቱ በቀጣይ አጭር ቀናት ውስጥ ከሊግ ኩባንያው ጋር የውል ስምምነት በማድረግ ወደ ስራ እንደሚገባም ታውቋል፡፡