Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የስራ ገበያ መረጃ ስርዓትን ማዘመንና መዘርጋት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣መስከረም 27 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የስራ ገበያ መረጃ ስርዓትን ማዘመንና መዘርጋት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ እና የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ናቸው።

በዚሁ ወቅት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደተናገሩት በአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነት ስራ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓታችን የዘመነ እና ቋታችን ሙሉ መሆን ይገባዋል ብለዋል።

የሚዘረጋው የሥራ ገበያ መረጃ አገልግሎት ዲጂታል ሲደረግ ፈታኝ እየሆነ የመጣውን የሥራ አጥነት ችግርና እሱ የሚያስከትለውን የከፋ ድህነት ትርጉም ባለው ደረጃ የማቃለል ሚና ይጫወታልም ነው ያሉት።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ በበኩላቸው÷ የዚህ ስምምነት መሠረቱና መነሻው ሀገራዊ ዲጂታል ስትራቴጂ ሲሆን ዲጂታል የአሰራር ስርዓት ተጠቃሚ ለመሆን የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ተቋምና አመራሩ ላሳየው ቁርጠኝነት አመስግነዋል።

ስምምነቱ በፊርማ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን የተጀመሩትን ለማጠናከር ያለቁትን ለማጠናቀቅ እንዲሁም አዲሱን ሲስተም ሥራ ላይ ለማዋል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግም አንስተዋል።

የሚተገበረው የስራ ገበያ መረጃ ሥርዓት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስራ ገበያ ጋር የተዛመዱ መረጃዎችን የመንግስት የግልና የማኅበራዊ ዘርፍ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በተቀናጀ ጥረት መረጃ በማሰባሰብ የለማ ዲጂታል ሥርዓት መፍጠር ይገባል ማለታቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version