Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አዲሱ የታጁራ ወደብ የብረት እና የድንጋይ ከሰል ገቢ ጭነቶችን እያስተናገደ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ አገልግሎት መስጠት በጀመረው አዲሱ የታጁራ ወደብ የድንጋይ ከሰል እና የብረት ገቢ ጭነቶችን በተቀላጠፈ መልኩ እያስተናገደ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ስፓር ካፔላ በተሰኘችውና ከደቡብ አፍሪካ 50 ሺህ ሜትሪክ ቶን የድንጋይ ከሰል ጭና በመጣችው መርከብ አገልግሎቱን የጀመረው ወደቡ ከስፓር ካፔላ በተጨማሪ ሁለት የድንጋይ ከሰል እና ሁለት የብረት መርከቦችን ጭነት ማስተናገዱ ተሰምቷል፡፡

ባለፈው ነሐሴ ወር ሸበሌ የተሰኘችው የኢባትሎአድ መርከብ ለታጁራ ወደብ የመጀመሪያ የሆነውን ከቱርክና ከዩክሬን ወደቦች የጫነችውን 25 ሺህ 492 ሜትሪክ ቶን ብረት አራግፋ መመለሷ ነው የተገለጸው፡፡

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ደግሞ ፊንፊኔ የተሰኘችው መርከብ ከሶስት የቱርክ ወደቦች የጫነችውን 25 ሺህ 382 ነጥብ 4 ሜትሪክ ቶን ብረት በታጁራ ወደብ በማራገፍ ላይ እንደምትገኝ ድርጅቱ ገልጻል፡፡

የታጁራን ወደብ ለድንጋይ ከሰል እና ለብረት ጭነቶች በቋሚነት ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑን የኢባትሎአድ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ የሽፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ካፒቴን ተፈራ በዳሳ ገልጸዋል፡፡

ካፒቴን ተፈራ ወደቡን እንደአማራጭ መጠቀም በተለይ የወጪና ገቢ ጭነቶችን በብዛት የሚያስተናግዱ የጅቡቲ ወደቦችን መጨናነቅ ይቀንሳል ብለዋል፡፡

ወደቡን በቀጣይ እንደአስፈላጊነቱ ለስንዴ ለማዳበሪያና ለስኳር ጭነቶች ማስተናገጃት ጥቅም ላይ የሚውል እና አቅምን የሚጨምር ተርሚናል መሆኑንም ካፕቴን ተፈራ ጨምረው መናገራቸውን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

Exit mobile version