አዲስ አበባ ፣ መስከረም 21 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ለዘመን ባንክ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በክፍያ ፈጻሚነት ለመሳተፍ የሚያስችለውን ዕውቅና ዛሬ ሰጠ፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ዑሌሮ ኡፒየው በተካሄደው የዕውቅና አሰጣጥ ስነ-ስርዓት ላይ በመገኘት የዕውቅና ሰርቲፊኬቱን ሰጥተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ የእውቅና ሰርተፍኬቱን በሰጡበት ወቅት ዘመን ባንክ ምርት ገበያው የሚጠይቀውን መስፈርት በማሟላት ዕውቅና እንደተሰጠው ገልጸው በምርት ገበያው በክፍያ ፈጻሚነት የሚሳተፉ ባንኮችን ቁጥር 17 መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘም በቀጣይ ባንኩ የቴክኖሎጂ አቅሙን ይበልጥ በማሳደግ በተገበያዮች መካካል ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆነ የገንዘብ ልውውጥ ተግባራዊ በማድረግ ስርዓቱን የማዘመን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡