አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ናይጀሪያ የኮሮና ቫይረስ ውጤትን ከ40 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ የሚያሳውቅ የመመርመሪያ ኪት መስራቷን አስታወቀች፡፡
አዲሱ መመርመሪያ ኪት በአነስተኛ ወጪና ስልጠና አገልግሎት መስጠት ይችላል ተብሏል፡፡
የሀገሪቱ የጤና ሚኒስትር ኦሉሩኒምቤ ማሞራ÷ አዲሱ መመርመሪያ አሁን በስራ ላይ ከሚገኘው ፒ ሲ አር ከተሰኘው የህክምና መሳሪያ በ10 እጥፍ ዋጋው ያነሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም አዲሱ መመርመሪያ ኪትን ስራ ላይ ለማዋል ከተቆጣጣሪው ባለስልጣን ፍቃድ እየተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡
መመርመሪያ ኪቱ የተሰራው በሀገሪቱ የህክምና ምርምር ተቋም ሲሆን ÷ናይጄሪያ የኮሮና ቫይረስን ለመዋጋት ለዓለም ከምታበረክታቸው ምርምሮች አንዱ መሆኑን ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡
ተስፋ የተጣለበት መመርመሪያ ከተቆጣጣሪው ባለስልጣን ማረጋገጫ ካገኘ በኋላ በመላው ሃገሪቱ እንደሚሰራጭ ተገልጿል፡፡
ናይጄሪያ ወደ 200 ሚሊየን ከሚጠጋ ህዝቧ ውስጥ እስካሁን 500 ሺህ ያህሉን ብቻ ነው ኮሮና ቫይረስ የመረመረችው ተብሏል፡፡
ከተመረመሩት ውስጥ 58 ሺህ ያህሉ ቫይረሱ ሲገኝባቸው 1 ሺህ የሚጠጉት ደግሞ ህይወታቸው ማለፉን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ምንጭ፥ቢቢሲ