አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ከኤሌክትሪክ መስመስር ዝርጋታ ጋር ተያይዞ በኤሌክትሪክ ሀይል እና በምድር ባቡር መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በመንግስት በኩል እልባት ተሰጠው።
390 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የባቡር ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው ከተጠናቀቀ እና ሙከራ ካደረገ በኋላ፥ በሃይል አቅርቦት አለመሟላት ምክንያት አገልግሎቱን በታሰበው ጊዜ መስጠት አልቻለም።
በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተፈጠረው አለመግባባትም ለፕሮጀክቱ የሃይል አቅርቦቱ በታሰበው ጊዜ እንዳይቀርብ አድርጎት ቆይቷል። ከሰሞኑም መንግስትም በጉዳዩ ላይ ጣልቃ የገባ ሲሆን፥ የፕሮጀክቱን የበጀት ጉዳይ መፍትሄ የሚሰጥ ውሳኔ አሳልፏል።
በዚህ መሰረትም ለፕሮጀክቱ ቀሪ ስራ መሸፈኛ የሚሆን ወጪ ከመንግስት ግምጃ ቤት እንዲሰጥና ለኃይል ማገናኛ መስመሮቹ የሚውል የግዢ ጨረታ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኩል ወጥቶ ስራው እንዲጀመር ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
በስምምነቱ መሰረትም የሚያስፈልገው ወጪ ከገንዘብ ሚኒስቴር ወጪ የሚደረግ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንም እዳውን ይከፍላል ተብሏል።
በሁለት ምዕራፍ ግንባታ 2007 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት አሁን ላይ ከአዋሽ ኮምቦልቻ ያለው የመጀመሪያው ምዕራፍ ሃዲድ ዝርጋታ በማጠናቀቅ ሙከራውን አከናውኗል።
ከሃይል አቅርቦቱ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል መስመሩ የፕሮጀክቱ አካል ስለሆነ ምድር ባቡር በጀት ሊመድብ ይገባዋል ሲል፤ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በበኩሉ ምላሹ ከተለመደው አሰራርና ከተፈራረምነው ውል ውጭ የተሰጠ ነው በሚል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይልን ምላሽ እንደማይቀበል መግለጹም ይታወሳል።
በዚህ ምክንያት ፕሮጀክቱ ስራ የሚጀምርበት ጊዜ ሲጓተት የሃዲዱ ክፍሎችም ለውድመትና ስርቆት መዳረጋቸውም ነው የሚነገረው።
ከአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ ለተገነባው የባቡር መስመር የኃይል ማስተላለፊያ ከፍተኛ መስመር፥ 37 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልገዋል።
በፍሬህይወት ሰፊው