አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የሱዳን ባለሀብቶች ልዑክ በአማራ ክልል ያካሄደው ጉብኝት አጠናቆ በኦሮሚያ ክልል ጉብኝት ለማድረግ ቢሾፍቱ ከተማ ገባ።
የባለሀብቶች ልዑክ ቢሾፍቱ ሲገባ የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ እና የሀገር ሽማግሌዎች አቀባበል አድርገውለታል።
በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት የቢሮ ሃላፊው እንደዚህ አይነት ጉብኝት ቱሪዝም ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ከማነቃቃት ባሻገር የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች አብሮነት እና ወንድማማችነት የበለጠ እንደሚያጠናከር ገልፀዋል።
የሱዳን ባለሀብቶች ልዑክ መሪ ኦማር አሊ በበኩላቸው የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝቦች በባህልም ሆነ በአኗኗር እንደ አንድ ህዝብ ናቸው ብለዋል።
በአማራ ክልል ጎርጎራን ጨምሮ የተለያዩ አካባቢዎችን የጎበኘው ልዑክ በኦሮሚያ ክልል በሚኖረው ቆይታም የቱሪዝም መዳረሻዎችን እና አማራጭ መስህቦችን ይጎበኛል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህም የአቢያታ ሻላ ሀይቅን፣ አዋሽ ፓርክ ፣ የባሌ ብሄራዊ ፓርክ እና ሌሎች የቱሪዝም መስህብ አማራጮች እንደሞጎበኝ ነው የተነገረው።
እነዚህ የሱዳን ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎችበሀገራቸው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ሲሆን ከጉብኝቱ በኋላ በጎበኟቸው አካባቢዎች በቱሪዝም ዘርፍ ኢንቨስት እንደሚያደርጉ ተነግሯል።
በብዙዓለም ቤኛ