አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የመስቀል ደመራ በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳቹ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመልዕክታቸው መስቀል የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታና የዕርቅ ተምሳሌት መሆኑን በመግለፅ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
መስቀል የመተሳሰብ በዓል እንደመሆኑ ካለን ላይ ለሌሎች በማካፈል በመተሳሰብ እናክብር ሲሉም አሳስበዋል፡፡
በዓሉ ከአዲስ አመት መግቢያ በኋላ ባማረ መስክና የአበቦች መዓዛ የሚከበር በመሆኑ ወቅቱን የሚያይ የታደለ ነው ሲሉም ነው የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
በዓሉ የሰላም፣ይቅርታና ፍቅር ምልክት እንደመሆኑ ስናከብረውም በመተሳሰብና መልካም በመስራት ይሁን በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ያለው ካለው ላይ ለሌለው ወገኑ በማካፈል፣ በነገሮች ሁሉ በጋራ በመቆም፣ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች እስኪቋቋሙ ድረስ የተቻለንን ድጋፍ እናድርግ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አቶ ሽመልስ አብዲሳ እስካሁን ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩትንም አመስግነዋል፡፡
በመጨረሻም የመስቀል ደመራ በአል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ከግንዛቤ በማስገባት በጥንቃቄ እንዲከበርም አሳስበዋል አቶ ሽመልስ፡፡
በተመሳሳይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የደመራ በዓል በአማራ ክልልና በመላው የሀገሪቱ ክፍል እንደ ጥምር በዓል የሚታይ ነው ብለዋል ፡፡
የኃይማኖታዊና ባህላዊ የአደባባይ ስርዓተ-ዐምልኮ የሚፈጸምበት፤ የሀገራችን ዘርፈ ብዙ ትውፊቶች እና ሚስጥራት የተገለጡበት ዓለማቀፋዊ ዕውቅና የተቸረው ዘመን ተሸጋሪ ክብረ-በዓል ነው ያሉት ፡፡
የመሰቀል ደመራ በዓልን ተከትለው የሚመጡ ህዝባዊ በዓላትም መሰረታቸውን ሳይለቁ በደስታ እንዲከበሩ ‹‹ ደመራን ስናከብር !! የመጣንበት የእሳት መንገድ በደመራ ችቦ ብርሃን እንዲያበቃ ህዝባችን ለጥምር ተልዕኮ መዘጋጀት እንደሚጠበቅበት የምናስገነዝብበት ጭምር ነው›› !! ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።