አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደመራ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በመላ ሀገሪቱ ተከበረ።
በዓሉ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ፣ ድሬደዋ ፣ ደብረ ማርቆስ ፣ አሶሳ ፣ ደብረ ታቦር ፣ ሀረር፣ ጅማ እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ነው የተከበረው።
በመስቀል አደባባይ በተከበረው በሚገኘው የደመራ በዓል ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ፣ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፣የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው፣ ዲፕሎማቶችና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ታድመዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር መስቀልን ባየን ቁጠር እግዚአብሔር ለኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር የምናስታውስበትና አዳኝነቱን፣ ፍቅሩን፣ ሰላሙንና አንድነትን የምናገኝበት መሆኑን መገንዘብ ይገባልም ብለዋል፡፡
“እኛም የመስቀልን ትረጉም ካወቅን ሰላምን፣ አንድነትን እንገኛለን፤ ወደ ሰላም ወደ ልማት እንጂ ወደ ጥፋት አንዳናተኩር ያደርገናል” ብለዋል አቡነ ማትያስ፡፡
‹‹ዛሬ የምናየው ድርጊት ከመስቀል ተቃራኒ ነው መነቃቀፍና መጠላላቱን ያስተማረን ማን ይሆን›› በማለት ሲያጠይቁ ሰውን መጥላትና መለያየት የኢትዮጵያውያን ሃሳብ አለመሆኑን ተናግረዋል ፡፡
ኢትዮጵያዊያን አብሮ መብላትና መኖርን ለዘመናት አካብተው የያዙ ቅዱስ ህዝብ ናቸው ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ፤ “የኢትዮጵያን ባህል ጥለን በጽንፍ የቆምን ልሂቃን ነን፤ ሰፊው ህዝብ ግን በሰላም በአንድነት መኖር የሚፈልግ ነው” ብለዋል፡፡
ሁሉም የፖለቲካ ልሂቃን በአንድነት ተመካክረው ችግሮችን እንዲፈቱ ጥሪ ሲያቀርቡ ወጣቶችም ጥያቄያችሁን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ አለባችሁ ሲሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ህዝቡ ከበዓሉ ባህልን፣ ሀይማኖትንና ስነ-ምግባርን በአንድነት አስተሳስሮ ስለመያዝ ልንማር ይገባል ብለዋል።
ቅዱስ መስቀሉን ለመደበቅ ቆሻሻ ይጣልበት የነበረ ቢሆንም አርነት የሚያወጣ እውነትንና ተግባርን ቀብሮ ማስቀረት እንደማይቻልም ጭምር ያስተምረናል።
“እኛም ብዙ የመዲናችችንን ገጽታ የሚያቆሽሹ ጉዳዮች ቢኖሩብንም እውነትንና ታማኝነትን ይዘን በአብሮነትና በፍቅር ተያይዘን በመስራት ጥላቻን አሽንፈን መውጣት አለብን” ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ።