Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኢትዮጵያ 75 ሚሊዮን ሰዎች ትኩረት ለሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች የተጋለጡ ናቸው – የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጤና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ 75 ሚሊዮን ሰዎች ትኩረት ለሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች የተጋለጡ መሆናቸውን ገለፀ፡፡

ሚኒስቴሩ ከትምህርትና ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴሮች እንዲሁም ከአጋር ድርጅቶች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር የሀሩራማ በሽታዎችን ለማጥፋት፣ ለመቆጣጠርና ለመከላከል የውይይት መድረክ አካሄዷል፡፡

በውይይት ላይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ የሴክተር ተቋማትና አጋር ድርጅቶች በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይ በውሃ አቅርቦትና ንፅህና አጠባበቅ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡

በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ሰለሞን 75 ሚሊዮን ሰዎች ለሀሩራማ በሽታዎች የተጋለጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች ከሚባሉት መካከል ዝሆኔ፣ ጊኒ ወርም፣ ቢልሃርዚያና ትራኮማ ይገኙበታል፡፡

እነዚህም የዓይን ብርሃን ማጣት፣ አካል ጉዳተኛነት፣ምርታማነት መቀነስና የትምህርት አቀባበል መቀነስን ያስከትላሉ፡፡

ዳይሬክተሯ እስካሁን ችግሩን ለመቀነስና ለመከላከል ህብረተሰቡን የማስተማር፣ የማከምና የመድሐኒት እደላ፣ የንፁህ ውሃ አቅርቦትን የማሻሻልና በሽታ አስተላላፊ ዘርፎችን የመቆጣጠር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች ከበሽታው ባሻገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናቸው ከፍተኛ በመሆኑ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር እንደሚሰራ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

Exit mobile version