አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጦር መሳሪያ ጨምሮ ሌሎች ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ፡፡
ከ18 ሚሊዮን 115 ሺህ 99 ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ከሆኑት መካከል ደረቅ ጫት፣ እህል፣ ትምባሆ እና ሌሎች ዕቃዎች በተለያዩ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ እና መቅረጫ ጣቢያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ነው የተነገረው፡፡
ከዚህ ውስጥ 13 ሚሊዮን 470 ሺህ ብር ግምታዊ ዋጋ ያለው ደረቅ ጫት ጭኖ ወደ ኬንያ ሲጓጓዝ የነበረ ተሸከርካሪ ያቤሎ የመቆጣጠሪያ ጣቢያ ገቢ መደረጉ ተገልጻል፡፡
ግምታዊ ዋጋቸው ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ የውጭ ሀገር ማሽላ እና ዘይት በቱሉጉሌድ እና ከቀብሪበያህ በኩል ሲገባ በጉምሩክ ሰራተኞች እና በፌዴራል ፖሊስ አባላት አማካኝነት በቁጥጥር ስር መዋሉ ተሰምቷል፡፡
እንዲሁም በኢትዮጵያ ለሚገኙ ለደቡብ ሱዳን ስደተኞች በእርዳታ የገባ ጠቅላላ ግምታዊ ዋጋው ከ1 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ማሽላ፣ ስንዴ እና አተር ክክ ከጋምቤላ ክልል ወደ አዲስ አበባ በህገ-ወጥ መንገድ በመጓጓዝ ላይ እያለ በጅማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስር በሚገኘው በሆሌና በባሮ ቀላ መቆጣጠሪያ ጣቢያ መያዙን ሚኒስቴሩ አስታውቋለ፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር ህብረተሰቡ ላደረገው ትብብር ምስጋናውን አቅርቦ በቀጣይም ተሳትፎው እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡