አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኮቪድ 19ን ለመከላከል የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን በ3 ሳምንታት ውስጥ ያሟሉ ትምህርት ቤቶች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ትምህርት መጀመር እንደሚችሉ ተገለፀ።
ትምህርት ቤቶችን ዳግም መክፈት በሚቻልበት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት በዛሬው እለት ውይይት ተካሂዷል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደው ውይይት ላይም የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ሚኒስትሮችም ተገኝተዋል።
ውይይቱ ትምህርት ቤቶችን ዳግም ለመክፈት ለውሳኔ የቀረበ ምክረ ሃሳብ፣ የ8ኛ እና 12ኛ ከፍል ብሄራዊ ፈተናና የግል ትምህርት ቤቶችን የትምህርት አሰጣጥ ሂደት የተመለከተ ነው።
የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ትምህርት ቤቶችን ዳግም ለመክፈት ስለቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ገለፃ አድርገዋል።
ባለፉት ሁለት ቀናት ከሁሉም ክልሎች የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ውይይት መካሄዱንና የውሳኔ ሃሳብም መቅረቡን አንስተዋል።
በዚሁ መሰረት የትምህርት ቤት አከፋፈት ሂደቱ በሶስት ዙር እንዲከናወን የሚል ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።
በዚሁ መሰረትም መሰረትም በገጠር ወረዳና ቀበሌ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመጀመሪያው ዙር ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም፣ በሁሉም የዞንና የክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በ2ኛ ዙር ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ እና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በ3ኛ ዙር ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት እንዲጀምሩ የውሳኔ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።
የዓለም የጤና ድርጅትና የጤና ሚኒስቴር ወረርሽኙን ለመከላከል ባስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ መሰረት ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው በፊት በመድሃኒት ማፅዳት፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልና የእጅ ማፅጃ ማሟላት እንዲሁም አካላዊ ርቀትን ማስተግበር ይጠበቅባቸዋል።
በዚህ መሰረት ኮቪድ 19ኝን ለመከላከል በ3 ሳምንታት ውስጥ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ያሟሉ ትምህርት ቤቶች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ትምህርት መጀመር ይችላሉ ተብሏል፡፡
ለሌላ አገልግሎት ውልው የነበሩ ትምህርት ቤቶችም አስፈላጊውን የማስተካከያ ስራ ሊሰራላቸው እንደሚገባም በውይይተ መድረኩ ተነስቷል።
እንደየ ትምህርት ቤቶቹ ነባራዊ ሁኔታ ትምህርት በፈረቃ እና አንድ ቀን በመዝለል ተራ ሊያስተምሩም ይችላሉ የተባለ ሲሆን፥ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት በአንድ ክፍል ውስጥ ከ20 እስከ 25 ተማሪ ማስተማር የሚችሉ መሆንም ይጠበቅባቸዋል።
በተያያዘ ዜና የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ህዳር 21፣ 22 እና 23፤ የ12ኛ ክፍል ፈተና ደግሞ ከህዳር 28 እስከ ታህሳስ 1 እንዲሰጥ የሚል ምክረ ሀሳብ ቀረቧል።
የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ላይ መቀመጥ የሚችሉት 7ኛ ክፍልን ተምረው ያጠናቀቁና የ8ኛ ክፍልን የአንደኛ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ ናቸው ተብሏል።
በተመሳሳይ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መውሰድ የሚችሉት የ11ኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀቁና የ12ኛ ክፍልን የመጀመሪያ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ እንደሆኑም ተገልጿል።