የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ ለግብርና ዘርፍ እድገት የ80 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

By Tibebu Kebede

September 24, 2020

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ እድገት ለመደገፍ የ80 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የድጋፉ ስምምነቱን የተፈራረሙት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ እና የአለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን ናቸው።

የአለም ባንክ ስራ አስፈፃሚ ቦርድ የባንኩ አንድ አካል የሆነው አለም አቀፉ የልማት ማህበር ለኢትዮጵያ 80 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንዲያደረግ ባሳለፍነው መስከረም 5 2013 ዓ.ም ውሳኔ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

የድጋፍ ስምምነቱም የባንኩ የስራ አስፈፃሚ ቦርድ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የተካሄደ ነው።

የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት የሚያተኩረው ግብርና ሚኒስቴር በሁለተኛ ግብርና ዕድገት ፕሮግራም በተለያዩ ክልሎች የአርሶ አደሮች ኑሮ እንዲያሻሻል የግብርና ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ፣ የተጨማሪ ገቢ ማገኘት የሚያስችላቸውና የግብርና ምርት ዕሴት ሰንሰለት እንዲጎለብት እየተገበረ ለነበሩ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ላይ ነው።

እንዲሁም የአነስተኛ አርሶ አደሮች የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያግዝ እንደሆነ መገለፁን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የዓለም ባንክ ግብርና ሚኒስቴር የአነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሮች ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያስችሉና በአጠቃላይ ድህነትን ለመቀነስ  የሚያካሂደውን የተለያዩ ዓይነት የልማት ፕሮግራሞች በገንዘብና በቴክኒክ እየደገፈ የሚገኝ መሆኑ ይታወሳል።