የሀገር ውስጥ ዜና

የመስቀል ደመራ በዓል የሚከበርበት የመስቀል አደባባይን የማፅዳት ስራ ተከናወነ

By Tibebu Kebede

September 24, 2020

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመስቀል ደመራ በአል የሚከበርበት የመስቀል አደባባይን በአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪነት ዛሬ ጠዋት የማጽዳት ስራ ተከናውኗል።

የደመራ ክብረ በዓል የማክበሪያ ስፍራ የጽዳት ዘመቻ ላይ የሀይማኖት አባቶችን ጨምሮ ከሁሉም ሀይማኖቶች የተውጣጡ ወጣቶች ፣ የጽዳት ሰራተኞች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

በጽዳት ዘመቻው ላይ የተሳተፉት የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ለደመራ በዓል ዝግጁ እንዲሆን ለማድረግ ቃል በገባው መሠረት በተባለው ጊዜ ዝግጁ በማድረጉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የደመራ ክብረ በዓል የከተማ አስተዳደሩ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በውስን የእምነቱ ተከታዮች ተሳታፊነት የሚከበር መሆኑንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሰክረተሪያት ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

የአዲስ አበባ ከተማ የከንቲባ ጽህፈት ቤት እና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ለመስቀል ደመራ እንዲደርስ ርብርብ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ምዕመናኑም የደመራ በአልን ሲያከብር እራሱን ከኮቪድ 19 በመጠበቅ መሆን እንዳለበትም አቶ ኤፍሬም በጽዳት ዘመቻው ወቅት ተናግረዋል።

የደመራ ክብረ በዓል የማክበሪያ ቦታውን የጸረ ተህዋስ ኬሚካል ርጭት በማድረግ የማጽዳት መርሃ ግብርም ተከናውኗል።