Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ኢትዮጵያውያን መብታቸው እንዲጠበቅ ለሊባኖሱ ፕሬዚዳንት መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2013(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለሊባኖስ ፕሬዚዳንት ማይክል ኦን በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን መብታቸው እንዲጠበቅ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
 
መልዕክቱን ቤይሩት የሚገኘው የኢፌዴሪ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ቆንሱል ጄኔራል አቶ ተመስገን ኡመር በሊባኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በአካል ተገኝተው ማስረከባቸው ነው የተገለጸው፡፡
 
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በመልዕክታቸው በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሰሩበት ደመወዝ እንዲከፈላቸው፣ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው አሳስበዋል፡፡

እንዲሁም ከሊባኖስ ወደ አገር ቤት መመለስ የሚልጉ የመኖሪያ ፍቃድ፣ ፓስፖርት ወይም የጉዞ ሰነድ የሌላቸው ዜጎች የመውጫ ቪዛ አስመልክቶ በሊባኖስ በኩል ውስብስብና ረጅም ጊዜ ስለሚወስድ የአሰጣጡ ሂደት ለተወሰነ ጊዜ ማሻሻያ እንዲደረግበት ጠይቀዋል፡፡

 
እንዲሁም ኢትዮጵያውያኑ ከቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት የሚሰጣቸውን የጉዞ ሰነድ በመያዝ ኤርፖርት በሚገኘው ኢሚግሬሽን በኩል መውጫ እየተመታ ወደ አገር ቤት መመለስ እንዲችሉ ሁኔታዎች እንዲመቻቹላቸው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
 
አቶ ተመስገን ኡመር ጉዳዩን አስመልክቶ ለሊባኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደርና የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ ለሆኑ ከፍተኛ ባለስልጣን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡
Exit mobile version