Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የሚያራምዱ የጋራ የፖለቲካ አቋሞቻቸው ላይ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ላይ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የሚያራምዱ የጋራ የፖለቲካ አቋሞቻቸው ላይ ስምምነት መፈራረማቸው ተገለጸ፡፡
 
ፓርቲዎቹ 10 ወራት ከፈጀው ውይይት በኋላ አብሮ ሊሰሩባቸው የተስማሙበት ነጥቦች ዙሪያ መግለጫ ተሰጥተዋል።
 
በመግለጫው ፓርቲዎቹ ለ10 ወራት ያህል በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲወያዩ ቆይተው በ10 ነጥቦች ላይ መስማማታቸው ተነግሯል።
 
ስምምነቱን የተፈራረሙት የኦሮሚያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት፤ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስ ኮንገረስ ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ውህደት ፣ የኦሮሚያ ብሄራዊ ፓርቲ፣ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ የመላ አማራ ህዝብ ፓርቲ ፣ ነፀብራቅ አማራ ድርጅት ፣ የአማራ ህልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ፣ የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት እና የአማራ ዴሞክራሲ ሃይል ንቅናቄ ናቸው።
ፓርቲዎቹ የጋራ መግባባት ላይ የደረሱባቸው ነጥቦችም፤
 
1. የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት ሁሉን አካታች የሆነ ቀጣይ ሀገራዊ ውይይትና ድርድር ማካሄድ፤
 
2. ጥርጣሬ፣ መከፋፈል፣ እርስበርስ መቃረን፣ ወደ ዳር መገፋፋት፣ አንዱ የሌላውን ስም ከማጥፋት እንዲሁም ሕዝብ ለሕዝብ ከሚያጋጩና ከሚያቃቅሩ ድርጊቶች መቆጠብ፤
 
3. ሀገራዊ የሕዝብ ቆጠራ ተዓማኒነትና ተቀባይነት ባለው አሠራር በማካሄድ የሁሉም የሀገሪቱ ብሔርና ብሔረሰቦች የህዝብ ብዛት በአግባቡ ተቆጥሮ እንዲታወቅ ማድረግ፤ የከዚህ በፊት ግድፈቶች የሚያርምና የማይደገምበት መሆኑን ማረጋገጥ፤
 
4. በሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት፣ የግልና የቡድን መብቶችን ማስከበርና በየጊዜውና በየደረጃው ነፃና ፍትሃዊ ምርጫን ማካሄድ፤
 
5. የኢትዮጵያ የታሪክ አቀራረብ የታሪክ አንጓዎችን ተከትሎ ከሁሉም ብሔርና ብሔረሰቦች በተውጣጡ የታሪክ ምሁራን የሀገሪቱን ሕዝቦች ግንኙነትና ታሪክ ጥናት እንዲካሄድ፤ የብሔረሰቦች ጥናት ተቋም (Institute) ማቋቋም፤
 
6. በኦሮሞና አማራ ክልሎች የሚኖሩ የሁሉም ሕዝቦች አባላት ደህንነትና መብቶች እንዲከበሩ፤
 
7. በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች ሰላምና ፀጥታ፣ ሕግና ፍትሕን ማስፈን፤ ከየቦታው ያለአግባብ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቄዬአቸውና ኑሮአቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ፤
 
8. ሀገሪቱ የምትተዳደርበት ሕገ-መንግስት ሁሉን አሳታፊ በሆነ መንገድ እንዲሻሻል ማድረግ፤
 
9. በሀገሪቱ ዘላቂና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ልማት ማጎልበት፤ የሕዝቦቻችንን ፍትሐዊ የኢኮኖሚና የሀብት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፤
 
10.የተለያዩ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችንና ትብብሮችን የሚያጠናክሩ ዝግጅቶችን በጋራ ማዘጋጀት መሆናቸው ተጠቁሟል።
 
ሁለቱ ወገኖች በበርካታ የእያንዳንዱን ሕዝብ ብሶትና አንገብጋቢ ጥያቄዎች በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አካሂደዋል፡፡
 
የተጠቀሱት የፖለቲካ አቋሞች ሁለቱ ወገኖች በጋራ የተስማማንባቸው ሲሆኑ፤ በተቀሩት ጉዳዮችም ላይ ተመሳሳይ ውይይቶችን ለመቀጠልና መላ ሕዝቦችንና አገሪቱን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሰፊና ሁሉን አቀፍ አገራዊ ምክክር እንዲደረግ ተስማምተዋል፡
Exit mobile version